News

Previous Next

በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት የዳያስፖራ ተሳትፎን ለማሳደግ የምክክር መድረክ ተካሄደ

 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የዳያስፖራ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ያሉ ማነቆዎችን መፍታትን ዒላማ ያደረገ የባለድርሻዎች የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ በአዳማ አካሂዷል። በምክክር መድረኩ ላይ ከዘጠኙ ክልሎቸ እና ሁለት የከተማ መስተዳድሮች የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች፣ የዳያስፖራ ማሕበራት አመራሮች፣ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ የዳያስፖራ ባለሀብቶች፣ በፌዴራል መስሪያ ቤቶች የዳያስፖራ ጉዳይ ላይ በኃላፊነት የሚሰሩ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ማነቆዎች የመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሁሉም ባለድርሻዎች ሚና ምን መሆን እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል። 

ይህ የምክክር መድረክ በክልል ደረጃ በተናጠል ሲካሄዱ የቆዩ የዳያስፖራ ተሳትፎን የማሳደግ ጥረቶችን በተናበበ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ግቦችን ሊያሳካ በሚችል መለኩ ለማቀናጀትም የታለመ ነው። በመድረኩ ላይም ይህን የቅንጅት ስራ መስመር ለማስያዝ የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ቀርቦ አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን መመሪያው በክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲፀድቅ እንደሚላክ ከስምምነት ተደርሷል።

በተጨማሪም በሀገር ቤት ያሉ የዳያስፖራ አባላት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥሪ በተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃግብር እንዲሳተፉ ተነሳሽነቱን ለመውሰድ የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በአዳማ ጎሮ በሚባለው አካባቢ የችግኝ ተከላ ፕሮግራምም አካሂደዋል።