News

የአንድነትና የሰላም ድልድይ ግንባታ ጉባኤ በለንደን ተካሄደ

በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የአንድነትና የሰላም ድልድይ ግንባታ ጉባኤ በለንደን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ አዘጋጅነት መጋቢት 8 ቀን 2011 በለንደን ተካሂዷል።

ጉባኤው በኢትዮጵያውያን መካከል የበለጠ መተማመንና መረዳዳትን ለማስረጽ፣ ጥላቻን ለመናድና በአገራቸው ጉዳይ በያገባኛልና በባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉ ሃሳብ ለመለዋወጥ ያለመ ነው።

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍስሃ ሻውል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ አሁን አቀፍ የለውጥ ሂደት ላይ ነች፤ለዚህ ለውጥ ቀጣይነት ደግሞ ዳያስፖራው የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

ኤምባሰው ከሁሉም ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጋር ተባብሮ ለመስራትና ለማገልገል ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ መሆኑን፤ ይህ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ጉባኤም የዚህ ቁርጠኝነት ጅማሬ ነው ብለዋል።

በእንግሊዝ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በገጽታ ግንባታና መሰል ዘርፎች የአገራቸው አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኤምባሲውም ዜጎች ለሚፈልጉት ሁሉንም አይነት አገልግሎት ለመስጠት ሁሌም በትጋት ለማገልገል መዘጋጀቱን አምባሳደር ፍስሃ ገልጸዋል።