News

Previous Next

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን ለመደገፍና ለማቋቋም የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰባቸው የሚያስመሰግን ተግባር እንደሆነ ተገለጸ፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኤምባሲዎች አስተባባሪነት ወገኖቻቸውን ለመደገፍና ለማቋቋም የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰባቸው የሚያስመሰግን ብቻ ሳይሆን የተቀደሰም ተግባር እንደሆነ ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት በቅርቡ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎችን ለመደገፍ በዩናይትድ ኪንግደም ለሦስት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው የበይነ መረብ የገቢ ማሰባሰበያ ዝግጅት ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም መንግስት ላለፉት ሁለት አመታት ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሂደት ውስጥ መግባቱን አስታውሰው በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት በፖለቲካ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ እያካሄደ ያለው ሪፎርም ባልተዋጠላቸው የውስጥና የውጭ አካላት ቅንብር በተገመደ ሴራ ህዝባችን ለችግርና ለጥፋት ሲዳረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡
በቅርቡም በህወሓት ጁንታ የሰሜኑን የአገራችንን ክፍል ሉኣላዊነት በማስከበር ላይ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በውድቅት ሌሊት የተፈፀመው ኢሰብኣዊ ድርጊት መላውን ህዝባችንን ያስቆጣ እኩይ ተግባር መሆኑን አንስተው፣ መንግስት ይህን ዘግናኝ ድርጊት በፈፀሙ የክህደት ሃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ ማስከበርና ሃገርን የመታደግ ተግባር አከናውኗል ብለዋል፡፡ በተደረገው ሁለገብ ርብርብም ጁንታው ፈጽሞ በማያገግም መልኩ ግብአተ መሬቱ መጠናቀቁና ርዝራዦቹም በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ህግ የማስከበር ሂደት በሰሜኑ የአገራችን ክፍልና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖች በፀረ ሰላም ሀይሉ በተነዛው ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳና ሆን ተብሎ በዚህ ሀይል በተፈጠሩ ግጭቶች ወገኖቻችን ከቤት ንብረተቸው መፈናቀላቸውንና ለስደት መዳረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሰራዊታችን ከዚህ ቀደም ካበረከቱት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ተፈናቃይ ዜጎቻችንን ለማቋቋም እያደረጉ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ መንግስት የጀመራቸውን ሪፎርሞች ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ ዳያስፖራው ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ወደሀገር ውስጥ በመላክ የጥቁር ገበያን የገንዘብ ዝውውርን ለማምከን በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላም በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ብርቱካን አያኖ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል ሀገራቸውን ለመደገፍ የገንዘብ ፣ የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ አሁንም የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለመርዳት ለሚያደርጉት የገንዘብ ማሰባሰብ ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትም በበኩላቸው የዳያስፖራውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንዲቻል መንግስት የዳያስፖራ ኤጀንሲን ማቋቋሙን ጠቅሰው፣ ኤጀንሲውም ከሴክተር ተቋማት ጋር በመቀናጀት የዳያስፖራውን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በትኩረት በማከናወን ላይ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ቅንጅታዊ አሰራሩም ዳያስፖራው የሀገሩን እድገትና ብልፅግና ለማፋጠን የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስገንዝበዋል፡፡ ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ዳያስፖራው ልዩ ልዩ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ እያሳየ ስላለው የተጠናከረ ተሳትፎ አመስግነው፣ ይኽው መልካም ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም የኢፌዴሪ አምባሳደር ክቡር ተፈሪ መለሰ ዳያስፖራው ሪፎርሙን በመደገፍ ከኤምባሲው ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለሀገራችን ብሄራዊ ጥቅሞች መከበርና ለወቅታዊ ጥሪዎች ምላሽ ለመስጠት በዳያስፖራው የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ግብረ ሀይል በዩናይትድ ኪንግደም አስተባባሪ አቶ ዘላለም ተሰማም በበኩላቸው ዳያስፖራው የተጀመረውን ሪፎርም ለመደገፍ አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸውን ከእንግሊዝ የኢፌዴሪ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡