News

Previous Next

በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ኤምባሲ የዳያስፖራ አገልግሎት ለሚሰጡ ዲፕሎማቶችና የአይሲቲ ባለሙያዎች በበይነ መረብ የዳያስፖራ መረጃ አያያዝ ስልጠና ተሰጠ

በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ኤምባሲ የዳያስፖራ አገልግሎት ለሚሰጡ ዲፕሎማቶችና የአይሲቲ ባለሙያዎች የዳያስፖራ መረጃን ለማጠናቀር እንዲያገለግል ከዚህ ቀደም ተዘጋጅቶ አገልግሎት ላይ ሳይውል በቆየውና በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ እንዲሁም አሜሪካን ሃገር በሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች በተሻሻለው የዳያስፖራ መረጃ ማጠናቀሪያ ዳታቤዝ ላይ በበይነ መረብ ስልጠና ተሰጠ፡፡
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ባስተላለፉት መልዕክት የዳያስፖራ መረጃን ማደራጀት ለኤጀንሲው ከተሰጡት ዋና ዋና ተግባርና ሃላፊነቶች መካከል አንዱ መሆኑን አንስተው፣ የመረጃ ማጠናቀሪያ ዳታቤዙን ወደስራ ለማስገባት ኤጀንሲው የሄደባቸውን ሂደቶች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ዳታቤዙ በቅድሚያ በክላስተር አስተባባሪ ሚሲዮኖች ከተሞከረ በኋላ ወደ ተግባር የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዳያስፖራ መረጃ ማጠናቀሪያ ዳታቤዝ አስፈላጊነትና ጠቀሜታን በተመለከተ በኤጀንሲው እንዲሁም የመረጃ ማጠናቀሪያ ዳታቤዙን አጠቃቀም በተመለከተ በአሜሪካን ሃገር በማይክሮሶፍት ኩባንያ ከፍተኛ የኮምፒዩተር ፕሮግራመር በሆኑት አቶ ደነቀው ጀምበሬ አማካኝነት የበይነ መረብ የተግባር ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ሰልጣኞች ላነሷቸው ጥያቄዎችም ምልሾችና ማብራሪያዎች ቀርበዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ም/ሚሲዮን መሪ የሆኑት ክቡር አቶ ሙሉጌታ ውለታው በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ባቀረቡት የመዝጊያ መልዕክት ከተጣበበ ጊዜያቸው ላይ መስዋዕት አድርገው ስልጠናውን ለሰጡትና ዕውቀታቸውን በበጎ ፈቃድ በማካፈል ላይ ያሉትን ትውልደ ኢትዮጵያዊውን አቶ ደነቀው ጀምበሬን አመስግነው፣ በተሰጠው የአቅም ግንባታ ስራ ላይ በመመስረት በቅድሚያ በሚሲዮናቸው ቀጥሎም ሚሲዮኑ በሚያስተባብራቸው ሚሲዮኖች ዳታቤዙን ወደ ስራ በማስገባት የተሻለ የዳያስፖራ መረጃ እንዲደራጅ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡