News

Previous Next

ከዐረብ ሃገር ኑሮ በመመለስና በስኬታማ የግብርና ሥራ ላይ በመሰማራት ለ100 ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠሩትን ፈቲያ መሐመድ ተዋወቋቸው።

በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት ሴቶች ውጣ ውረዶች ይገጥሟቸውና

ከሚዘፈቁባቸው ችግሮች ደግሞ ሳይወጡ የሚዘልቁም ይኖራሉ።

የፈቲያ መሐመድ ተሞክሮ ግን ከብዙዎች ለየት ያለ ነው።

ፈቲያ በምሥራቅ ሐረርጌ በባቢሌ ወረዳ፤ በየረር ወንዝ ዙሪያ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርታ ትገኛለች፡፡

 

ሰሜ ፈቲያ መሐመድ ነው፤ የተወለድኩትም በምሥራቅ ሐረርጌ በባቢሌ ወረዳ ሲሆን

 12 ዓመቴ ቤተሰቦቼ ለአንድ ዐረብ ዳሩኝ።

 ይህ ከሳዑዲ ዐረብያ የመጣው ሰው ብዙ ገንዘብ ነበረው። እዚያም 28 ዓመታት ኖርኩኝ።

 28 ዓመታት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩት ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር።

 ያንን ሁሉ ጊዜ ዐረብ ሃገር ስኖር ስለ ኢትዮጵያ ጥሩ ነገር ሰምቼ አላውቅም።

 ኢትዮጵያን በረሃብና በስቃይ ነው የሚገልጿት።

እኔንም 'ከረሃብ ሃገር ነው የመጣሽውሲሉኝ ውስጤ በጣም የይታመም ነበር።

 እኔ ግን ሃገሬን የማውቃት በተፈጥሮ ሃብት የተሸለመች በመሆኗ ነው። 

ስለ ድህነቴ በሚሰድቡኝ ጊዜ በዓይኔ የሚሄድብኝ ዙሪያው ለምለም የሆነው ቀዬ ነው።

ሃገራቸው አሸዋ እንጂ ለሰብል የሚሆን መሬት እንኳን የለም።

 ከአሸዋው ውስጥ የሞቀ ውሃ አውጥተው አቀዝቅዘው እና አፈር ደግሞ ከሌላ ሃገር እያሰመጡ ነው የሚጠቀሙት። 

ሃገሬ ግን በተሄደበት ቦታ ሁሉ የተሰጣትን የምታፈራ ሃገር ናት።

 ይህም ነው ለሁሉም ነገር መነሻ የሆነኝ።

የቅንጦት ኑሮ ትቼ ገንዘቤን መቋጠር ጀመርኩኝ። እጄ የሚገባውን ገንዘብ በሙሉ እቀብረው ነበር። በዚህ መልኩ ብሬን ሰብስቤ ወደ 20 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ሲጠጋልኝ ቀልቤ ወደ 'ሃገርሽ ተመልሽአለኝ። 

ብሬን ቋጥሬ ወደዚህ ለመምጣት በቆረጥኩበት ሰዓት የኢትዮጵያ መንግሥት ሰው በሃገሩ ሠርቶ እንዲበለጽግ ጥሪ እያቀረበ ነበር።

 

እኔም ያንን ዕድል በመጠቀም ማድረግ ስለምፈልገው ኢንቨስትመንት ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤ ጥያቄዬን አቀረብኩኝ። በኢትዮጵያ መንግሥት ጋባዥነት 1998 . ወደ ሃገር ቤት ተምልሼ ለሥራዬ ሁኔታዎችን አመቻቸሁኝ።

1999 ወደ ኢትዯጵያ ስመለስ መንግሥት አዲስ አበባ አካባቢ ኢንቨስት እንዳደርግ መሬት ሰጥቶኝ ነበር። 

እኔ ግን በተወለድኩበት አካባቢ ነበር ለውጥ ማምጣት የምፈልገው።

የተቸገረን መርዳት፣ የተጠማን ማጠጣትና የተራበን ማብላት ትልቁ ሕልሜ ነበር። መንግሥት ግን 'አንቺ ሴት ነሽ፣ ብዙ ገንዘብም ይዘሻል።

 መሬት ሰጥተንሽ እዚሁ አዲስ አካባቢ ብትሆኚ ነው የሚሻለውአለኝ።

 

"ወይ እንደ እኔ ትሆናላችሁ ወይ እንደ እናንተ እሆናለሁ"

የተወለድኩበት አገር ህዝብ ውሃ ላይ ተኝቶ ይጠማል፣ ለም አፈር ላይ ተቀምጦ ይራባል።

 ለዚህ ነው ይህንን ሕዝብ መጥቀም እንደምፈልግ ለመንግሥት ያሳወቅኩት። ሆዴን በጣም የሚበላው ነገር የባቢሌና የሐረርጌ ሕዝብ ወንዝ በመንደሩ እያቋረጠ መጠማቱ ነው።

እንደ እነ ግብፅ፣ ሱዳንና ሳዑዲ ዐረብያ ያሉ አገራትን አይቼም እውቀት ቀስምያለሁ። ባገኘሁትም ልምድ የአገሬን ሕዝብ ኑሮ መቀየር እንደምችል አምን ነበር። 

መጀመሪያ ወደ ባቢሌ ስመጣ ምድሩ አቀቅበትና ቁልቁለት እንዲሁም ጋራና ገደል የበዛበት ነበር። ሰዎች በቆሎ ከሚያበቅሉባቸው ትንንሽ ማሳዎች ውጪ ምንም አልነበረም።

በወቅቱ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ያሉ ሁሉም የመንግሥት መዋቅሮች ድጋፍ አድርገውልኛል። 

ከመጣሁ ጊዜ አንስቶ የመንግሥት ልማት ቢሮ የሞራል ድጋፍ በማድረግ ለስኬቴ ምክንያት ሆኗል።

 

የኤረር ወንዝ ባለበት አካባቢ መሬት ከተፈቀደልኝ ወዲህ ከውጪ ሃገር ትራክተሮችንና የእርሻ መሣሪያዎችን በማስመጣት ሥራውን አንድ ብዬ ተያያዝኩት።

 ያንን ጋራና ገደል ደልድሎ የእርሻ መሬት ማድረግ በጣም ከባድ ነበር። 

ዶዘርና ግሬደር ሚሊዮን ብር ተከራይቼ ቦታውን ሜዳ አደረግኩት።

መሬቱን ካደላደልኩኝ በኋላ እንዴት ዉሃ ከከርሰ ምድሩ ማውጣት እንደምችል ማሰብ ጀመርኩኝ። 

ይህንን ያስበኩት ደግሞ ለእራሴ ብቻ ሳይሆን ለሕዝቡም ብዬ ነበር። ውሃ በማውጣት ልምድ ያላቸውን ሰዎች ከሱዳን በማምጣት ማሠራት ጀምረኩ። 

ይህን ሳደርግ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፍቃድ አውጥቼ እና እነርሱን በዶላር ከፍዬ ነበር።

እነርሱም በአንድ ቀን ውስጥ ከጉድጓድ ውሃ ማውጣት ይችሉበታል።

 እግረ መንገዳቸውን 50 ወጣቶችን እንዲያሰለጥኑ አደረግኩኝ። ሥልጠናውን የወሰዱት ወጣቶችም በአካባቢው ላሉ ብዙ ሰዎች ዉሃ አውጥተዋል።

 በዚህ አጋጣሚ የባቢሌ አካባቢ ሰዎች ይገጥማቸው የነበረው የውሃ ችግር ተፈቷል ለማለት ይቻላል።

ለእኔ ሕዝቤን ውሃ ማጠጣት ትልቅ ደስታ ነው። ውሃ በማግኘቴ እኔም ማሳዬን አስፍቼ እያለማሁ ነው።

 እስካሁን 5ሺህ ማንጎ፣ 5ሺህ ብርቱካን፣ 30 ሺህ ፓፓዬ፣ 1ሺህ ዜይቱን፣ 2200 ቡና እና 2 ሺህ ሽፈራው (ሞሪናጋየሚባል ዘር ተክያለሁ።

 

የዚህ አካባቢ ሰው ንፁህ የመጠጥ ውሃ በማግኘቱ ተጠቅሟል።

 ደግሞም በማሳዬ መሥራት መተዳደሪያቸው የሆነላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተወጣጡ ሰዎች ይሠሩበታል።

እስካሁን 100 የሚሆኑ ሰዎች ይሰራሉ፤ በቋሚነት ደግሞ 60 እስከ 70 የሚሆኑ ሰዎች በዚህ ማሳ ይሠራሉ። 

ቤተሰብ አፍርተው እዚሁ የሚኖሩም ብዙ ናቸው። 

በአጠቃላይ የአካባቢው ሕዝብ ማሳውን እንደራሱ ንብረት ነው የሚጠቀምበት። በተለይ ሴቶች እንደፈለጉ አምርተውና ሽጠው እንዲጠቀሙ ፈቅጄላቸዋለሁ።

እስካሁንም በሠራኋቸው ሥራዎች ዋንጫና ሜዳልያ ጨምሮ ብዙ ሽልማቶች ተሰጥተውኛል።

 ሕዝብ በተፈናቀለበት ጊዜ ረብሻ ስለነበረ ሥራችን ላይ እንቅፋት ገጥሞን የነበረ ቢሆንም ሥራችንን ግን አላቋረጥንም ነበር።

አሁን ሕዝብ የሚጠቀምበት አንድ የጭነት ፒክ አፕ እና አንድ አይሱዙ አለኝ።

 እኔ ደግሞ የእራሴ የቤት መኪና እና ደረጃውን የጠበቀ ቤት በዚሁ በማሳዬ መካከል ሠርቼ እየኖርኩኝ ነው።

ልጆቼ በሙሉ በሳዑዲ ዐረብያ የእራሳቸውን ቤተሰብ መሥርተው እየኖሩ ነው። 

ባለቤቴ ሞቷል ልጆቼና የባለቤቴ ዘመዶች መጥተው ማሳዬን በጎበኙ ጊዜ በኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት ቦታ አለ ብሎ ለማመን ከብዷቸው በጣም ተደንቀው ነበር።

የያዝኩት ማሳ ሰፊ ነው። ስለዚህ ዓላማዬ ይህንን ሰፊ ማሳ መሙላት፣ እያለሙ መንከባከብ እና በብዛት ለገበያ ማቅረብ ነው። 

ቀጥዬም ፋብሪካ አቋቁሜ ከፍራፍሬዎቹ የተለያዩ ምርቶች ማውጣት ነው። 

እዚያው ማሳዬም ላይ ለፋብሪካው የሚሆን ቦታ አስቀምጫለሁ።

ለሴቶች አስረግጬ መንገር የምፈልገው ሁሉን ነገር የመሥራት ችሎታ እንዳላቸው ነው። 

ቆርጠው ከተነሱ ደግሞ ማንኛውንም ነገር ከግብ ማድረስ እንደሚችሉ አምናለሁ።

 አብዛኛዎቹ ግን ብከስርስ ብለው በመስጋት ያመነታሉ። አንድን ሥራ ሳትጅምሪው ለፍርሃት እጅ ከሰጠሽ በጭራሽ ስኬታማ መሆን አይቻልም።

ስለዚህ ሴቶች ቆራጥ፣ በእራሳቸው የሚተማመኑ እና ጠንካራ አቋም ካላቸው የሚፈልጉበት ቦታ ይደርሳሉ። 

የምንሠራውንና ወደ ስኬታችን የሚያሻግሩንን ነገሮች ለይተን ማወቅ አለብን።

በተለይ ዐረብ ሃገር የሚኖሩ ሴቶች እዚያ መዝናናቱን ትተው ለወደፊታቸውና ለሃገራቸው የሚጠቅማቸውን ነገር ለመሥራት ማቅድ ይኖርባቸዋል፤ ለነገ ማሰብ አለባቸው።