News

በተያዘው በጀት ዓመት ዳያስፖራው ወደ አገሩ ከሚልከው ገንዘብ 4 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ መታቀዱን ኢ.ዜ.አ. ዘገበ።

በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት ዳያስፖራው ወደ አገሩ ከሚልከው ገንዘብ 4 ቢሊዮን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ 50 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም ገልጿል።

የዓለም ባንክ ባደረገው ጥናት እ.አ.አ በ2019 በተለያዩ የዓለም አገሮች የሚኖሩ ዜጎች ወደ አገራቸው 712 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ (ሬሚታንስ) መላካቸውን ገልጿል።

አብዛኛው ገንዘብም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገራት የተላከ መሆኑንም አመልክቷል።

ይኽው መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ከሚገኙ ዘጠኝ ሰዎች አንዱ ከሬሚታንስ በሚገኝ ገንዘብ ድጋፍ የሚያገኝ ሲሆን በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ዜጎችም በወር በአማካይ ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ወደ አገራቸው ይልካሉ።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ አፍሪካዊያን 48 ቢሊዮን ዶላር የላኩ ሲሆን ናይጄሪያ፣ጋና ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን በዋንኛነት ገንዘቡ ከተለካባቸው አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

ከሦስት እስከ አምስት ሚሊዮን ዜጎቿ በተለያዩ የዓለም አገራት ይኖራሉ ተብሎ የምትገመተው ኢትዮጵያም ዜጎቿ በተለያዩ የፋይናንስ አማራጮች ገንዘባቸውን ወደ አገራቸው ይልካሉ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ዳያስፖራው ወደ አገር ውስጥ ከሚልከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) 4 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የታቀደው ዕቅድ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሬሚታንስ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ያስገባና ለዚህም ዳያስፖራው ሕጋዊ አማራጮችን ተጠቅሞ ወደ አገሩ ገንዘቡን እንዲልክ የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

“በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የባንክ ቅርንጫፎችን የመክፈትና ሕጋዊ አሰራሮችን ተግባራዊ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ ነው” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ገንዘብ ሁሉም ሬሚታንስ ተብሎ እንደሚቀመጥና ኤጀንሲው ከዚህ ውስጥ ዳያስፖራው ወደ አገሩ የላከውን ገንዘብ ከባንኩ ጋር በመሆን የመለየት ተግባር በመከናወን ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የመለየት ተግባሩ ዳያስፖራው ለግለሰብ የሚልከውንና የዳያስፖራ ድርጅት አገር ውስጥ ለሚገኝ ድርጅት የሚልከውን ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል። 

የአዲሱ የብር ኖት መቀየርም ሕገወጥ የገንዘብ አላላክ ሂደት አፍርሶ ህጋዊ የፋይናስ አሰራርን ለመከተል ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሰማራ የተለያዩ አማራጮችንና እድሎችን የማስተዋወቅ እንዲሁም ወደ አገር ቤት በሚመጣበት ወቅት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከተቋቋመባቸው አላማዎች መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

በ2013 በጀት ዓመትም 50 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ ኤጀንሲው እቅድ መያዙን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት። 

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ 300 ዳያስፖራዎች  በተለያዩ መስኮች ሊሰማሩባቸው የሚችሉባቸውን አማራጮች በአካል መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ዳያስፖራዎቹ ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ሰሜን አሜሪካና አፍሪካ የመጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ግብርና፣ ቱሪዝምና አምራች ዘርፍ ዳያስፖራዎቹ ወደ ሥራ ቢገቡባቸው ውጤታማ ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ መስኮች እንደሆኑና በሚያገኙት ጥቅም ላይ ገለጻ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም አመልክተዋል።

“ዳያስፖራው አማራጮችን ያያል፤ ፍላጎት አለው ማለት ሁሉም መዋዕለ ንዋዩን ያፈሳል ማለት አይደለም” ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት፣ በተጨባጭ የመስራት ፍላጎት ያላቸው ወደ ኢንቨስትመንት እንደሚገቡ አመልክተዋል።

አንድ ዳያስፖራ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ስራ መግባት ከፈለገ ለፕሮጀክቱ ከሚያወጣው ካፓታል 25 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንዳለበትም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እያፈሰሱ ያሉ ዳያስፖራዎች ያቋቋሟቸው ማህበራት በአሁኑ ወቅት በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ላሳዩ ዳያስፖራዎች ተሞክሯቸውን እያካፈሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ መዘግየትና ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዳያስፖራው ሊፈቱ ይገባል ብሎ ያነሳቸው ተግዳሮቶች እንደሆኑም ገልጸዋል።

የተጠቀሱት ችግሮች ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እንዲበጅላቸው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ወይዘሮ ሰላማዊት አመልክተዋል።

መንግስት ሰላምና ደህንነትን ለማስከበር በትኩረት እየሰራ መሆኑንና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መዘግየት እንዳይኖር በየጊዜው እየተፈተሸ የመፍትሔ  እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና በሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የልማት ስራዎች የዳያስፖራውን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲሁም መብታቸው እንዲጠበቅ ተልዕኮ ተሰጥቶት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በመጋቢት 2011 ዓ.ም ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል።

በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት አጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ ከተላከው 8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላሩ ከዳያስፖራዎች የተላከ መሆኑን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

እ.አ.አ በ2020 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢኮኖሚ ላይ ባሳደረው ጫና ምክንያት ከውጭ አገር የሚላክ ገንዘብ መጠን (ሬሚታንስ) በ20 በመቶ እንደሚቀንስ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ያሳያል።