News

Previous Next

በባህሬን ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ተካሄደ

 

በኢ... ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ክብርት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራውና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር / ሰላማዊት ዳዊትን ያካተተው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በባሕሬን ከሚኖሩ 350 በላይ ከሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ጋር በዜጎች መብትና ደኅንነት መከበር እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ውይይት አካሄደ።

 

ይህ ውይይት ቀደም ሲል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ከተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ከባህሬን ከመጡ ዜጎቻችን የተነሱትን ችግሮች በመለየት የመፍትሄ ሐሳቦችን ለመስጠት እና በባሕሬን በሚኖሩ ዜጎቻችን እና የኢ... የክብር ቆንስላ /ቤቱ መካከል አሉ የተባሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት እንዲሁም የኢትዮጵያውያኑን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ከባሕሬን መንግሥት ጋር በመነጋገር የቆንስላ ጄኔራል ቤት የሚከፈትበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ለልዑካን ቡድኑ በሰጡት መመሪያ መሠረት የተከናወነ ነው፡፡

 

ከዚህ የውይይት መድረክ ቀደም ብሎ የልዑካን ቡድኑ ከክብር ቆንስላ /ቤቱ ኃላፊና ሠራተኞች፣ ከሐይማኖት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና በደል ደርሶብናል ከሚሉ የማህበረሰቡ አባላት ጋር የተለያዩ የተናጠልና የጋራ ውይይቶችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በውይይቶቹ በዜጎች ላይ እያጋጠመው ያሉ ችግርች ከመለየታቸውም ባሻገር ከባህሬን መንግሥት አካላት ጋር በሚደረግ ውይይትም የሚነሱ ጉዳዮችን ከመለየታቸው በተጨማሪ ከባህሬን ከፍተኛ የመንግስት አካላት ጋር ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

 

ይህንን መነሻ በማድረግም ከኢትዮጵያውያኑ የዲያስፖራ አባላት ጋር ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በውይይቱም የክብር ቆንስላ /ቤቱ አገልግሎት አሠጣጥ በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑን፣ በባሕሬን ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በክብር ቆንስላው የሚሰጠው አገልግሎት ተደራሽ አለመሆኑን፣ /ቤቱ በባሕሬን የሚኖሩ ዜጎቻችንን መብት፣ ጥቅምና ክብር በተሟላ መልኩ ያላስጠበቀ መሆኑን፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ ኢትዮጵያውያን የመብት ጥሰት የሚደርስባቸው መሆኑንና ይህንንም ለመከላከል የክብር ቆንስላው አቅም ውስን በመሆኑ በመንግሥት በኩል የቆንስላ ጄኔራል ቤት መከፈት ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በክብር ቆንስላ /ቤቱ ኃላፊና በአካባቢው ነዋሪ ዜጋችን መካከል የተነሳውን አለመግባባት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር / አብይ በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ባካሄዱት ውይይት ወቅት በእርቅ የፈቱት ቢሆንም እርቁን ወደመሬት ለማውረድና ተምሳሌታዊ ለማድረግ በዕለቱ የሐይማኖት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሕዝቡ ባለበት አጠቃላይ የእርቀ ሰላም ኘሮግራም ተካሂዷል፡፡

 

በመጨረሻም በባሕሬን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች እርስ በእርስ የሚረዳዱበት፣ መረጃ የሚለዋወጡበትና በሀገራቸው የልማት እንቅስቃሴዎች የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉበት አደረጃጀት መመስረት የሚያስፈልግ በመሆኑ በባሕሬን የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማህበር ለማቋቋም የሚያመቻቹ ከሁሉም የእምነት ተቋማት ተወካዮች፣ ከታዋቂ ግለስቦች፣ ከወጣቶችና ከሴቶች የተውጣጡ 9 ( ዘጠኝ) አባላት ያሉት አደራጅ ኮሚቴ በህዝቡ ፍላጎት መመረጡን በኩዌት የኢፌዲሪ ኤምባሲ ዘግቧል ፡፡