News

Previous Next

ባንኩ በውጪ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ተባለ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አለም አቀፍ ተደራሽነቱን በማስፋት በውጪ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ተገለፀ፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ የአብስራ ከበደ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ባንኩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ያሉባቸው የውጭ ሀገራት አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት ቅርንጫፎችን እየከፈተ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈትም ጥናት እያደረገ ነው፡፡

 

በአሁኑ ሰአት በአዋጭነት ጥናቱ መሰረት በደቡብ ሱዳንና በጁቡቲ የተከፈቱ ቅርንጫፎች በርካታ ኢትዮጵያውያን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን አቶ የአብስራ ተናግረዋል።

እንደ አቶ የአብስራ ገለፃ፣ በውጭ ሀገራት የሚከፈቱ ቅርንጫፎች የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የንግድ ግንኙነት የሚያጠናክርና የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በተለይ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሟላ የባንክ አገልገሎት እንዲያገኙ ያደርጋል።

በቅርቡ በጁቡቲ የተከፈተው ቅርንጫፍ በሁለቱም አገራት ያለ ዘርፈብዙ ስትራተጂካዊ ግንኙነትን የበለጠ እንደሚያጠናክር ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ቅርንጫፎች ሲከፈቱ ከአዋጭነቱ በተጨማሪ ህብረተሰቡን ተደራሽነት የማድረግ ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን የጠቆሙት አቶ የአብስራ ደቡብ ሱዳን ጁባ ላይ የተከፈተው ቅርንጫፍ ለበርካታ ዜጎች አገልግሎት እየሰጠ ከመሆኑ የተነሳ ውጤታማ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባንኩ በውጭ ሀገር ቅርንጫፎችን ሲከፍት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑን የተናገሩት አቶ የአብስራ የአካባቢውን ባህል፣ወግና ቋንቋ የሚያውቁ እንዲሁም ለስራው የሚመጥን የትምህርት ዝግጅት ያላቸው የሃገሪቱ ዜጎች አብረው እንደሚቀጠሩም ገልፀዋል።

 

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት