News

Previous Next

ዶቼ ሆህሹለ ፎር ሜዲሲን የህክምና ኮሌጅ ከባለድርሻ አካላት ጋር የትውውቅ ፕሮግራም አካሄደ

በጀርመን ሃገር ነዋሪ በሆኑት ወ/ት መሰረት አምባው የተቋቋመው ዶቼ ሆህሹለ ፎር ሜዲሲን የህክምና ኮሌጅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር ከተማ የትውውቅ ፕሮግራም አካሄደ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፣ በተጋባዥ እንግዳውና በኮሌጁ ባለቤት መልዕክቶች ተላልፈዋል። የዕለቱ የክብር እንግዳና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ ባለሃብቷ የተወለዱበት አካባቢ ያለበትን ችግር ተረድተውና መፍትሔ የሚሆን ዕቅድ ይዘው ለማልማት በመምጣታቸው አመስግነው፣ ሌሎችም የእሳቸውን አርአያ እንዲከተሉ ጋብዘዋል። ምክትል ከንቲባው አክለውም ከተማ አስተዳድራቸው የዳያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማገዝ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። የድርጅቱ መስራችና ባለቤት ወ/ት መሰረትም በበኩላቸው የክልሉ ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ላደረገላቸው ትብብር ምስጋናቸውን ገልጸው፣ የትውውቅ ፕሮግራሙ ያስፈለገበትን ምክንያት በዝርዝር አቅርበዋል። ከነዚህም መካከል ኮሌጁን ከባለድርሻ አካላት ጋር ማስተዋወቅ፣ ኮሌጁ የህክምና ዶክተሮችን የሚያሰለጥን እንደመሆኑ መጠን በጤናው ዘርፍ በክልሉ ብሎም በሃገር አቀፍ ደረጃ ሊያሳካ ያቀዳቸውን ዓላማዎች ማጋራት እንዲሁም በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሚኖር ግንኙነት መሰረት መጣል የሚሉት ይገኙበታል።

ኮሌጁ ለጊዜው በተከራየው ባለአምስት ፎቅ ህንጻ ውስጥ ስራውን ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ከመጪው የፈረንጆች አዲስ አመት ጀምሮ የማስተማር ስራውን እንደሚጀምር ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ ባለሃብቷ በባሕር ዳር ከተማ የማስተማሪያ ሆስፒታል የመገንባት ዕቅድ እንዳላቸው ታውቋል።

ባለሃብቷ በጀርመን ሃገር በጥብቅና እና በሕግ ማማከር ስራ የሚተዳደሩ ሲሆኑ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ በሃገራቸው በጤናው ዘርፍ የሚታየውን ችግር የመፍታት ህልም እንደነበራቸው ይናገራሉ።