News

Previous Next

ክብርት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንን አወያዩ

በ28ኛው 'የዓለም የምጣኔ ሃብት ፎረም ለአፍሪካ' ለመሳተፍ ደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን የሚገኙት ክብርት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንን በተወካዮቻቸው አማካይነት ሴፕቴምበር 4 ቀን 2019 በኬፕ ታውን አወያይተዋል።

ውይይቱ በዋነኛነት ኢትዮጵያዊያኑ በደቡብ አፍሪካ በሚገጥሟቸው ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ የተካሄደ ሲሆን ክብርት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ከተሰብሳቢዎቹ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሸና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህ ረገድ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያለን የሁለትዮሽ ግንኙነት ጠንካራና ስትራቴጂክ የሚባል እንደሆነ ተናግረው ይህን ዕድል በመጠቀም በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ ዜጎቻችንን ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስ በመንግስት በኩል እንደሚስራ ገልጸዋል። ግንኙነቱን ለማጠናከር ይበልጥ መስራት ለዜጎቻችን ጥቅሞች መከበር ያለውን አስተዋጽኦ አስረድተው የሰዎች ነጻ ዝውውርና ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖች እንዲከበሩ እንደሚሰራም አንስተዋል። ኢትዮጵያዊያኑ ያነሷቸው ጥያቄዎችም አንድ በአንድ እንደሚታዩም ተናግረዋል። ኢትዮጰያዊያን በሀገር ጉዳይ ላይ ያላቸውን ኣንድነት ጠብቀው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያዊያኑ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያሉትን የሪፎርም ስራዎች እንደሚከታተሉና ወጤታማ ይሆኑ ዘንድም ደጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በደቡብ አፍሪካ ከደህንነትና ከጸጥታ አኳያ ያለባቸውን ስጋትና ተግዳሮት ገልጸው የኢትዮጵያ መንግስት ከደቡብ አፍሪካ መንግስት ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በአፍሪካዊያን ላይ የሚደርሰው ዘር-ተኮር ጥቃት እንዲቆም የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። አያይዘውም የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ የተከሰተውን ዘር-ተኮር ጥቃት ተከትሎ ድርጊቱን በመግለጫ በማውገዙና ጥቃቱን የፈጸሙት ግለሰቦችም ልፍትህ እንዲቀርቡ እንዲደረግ ጥሪ በማቅረቡ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያኑ የስራና የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ያለባቸው ተግዳሮት ሀብት ንብረታቸውን ህጋዊ ለማድረግና እንዳይችሉና ለሌሎች ዘርፈ-ብዙ ችግሮች እንዳጋለጣቸው ተናግረዋል።

ከኤምባሲ አገልግሎት ተደራሽነት አኳያ ከፕሪቶሪያ ኤምባሲ በተጨማሪ በሌሎች የደቡብ አፍሪካ አካባቢዎችም የቆንስላ ጽ/ቤቶች እንዲከፈቱ ጠይቀዋል።

በውይይቱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ የተገኙ ሲሆን በተለይም ዳያሰፖራው ከሀገራችን እድገትና ለውጥ ተጠቃሚ በሚሆነባቸው ጉዳዮቸ ዙሪያ ሀሳብ ሰጥትዋል። በፋይናንሱ ሴክተር የዳያስፖራውን ሙሉ ተሳታፊነት ለማረጋገጥ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎችንም አብራርተዋል። ሌሎች የፖሊሲ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በተመለከተ በከፍተኛ የመንግስት አካላት ደረጃ ውይይት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያም በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያኑ ያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን ተቀብለው ከአጭር ጊዜ አኳያ መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚችሉ ጉዳዮች ተለይተው በተፋጠነ ሁኔታ እንደሚሰራባቸው ገልጸው ለሌሎች ጥያቄዎች ደግሞ በደቡበ እፍሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያዊያን አደረጃጀቶች ጋር በመሆን በጥናት ላይ በመመስረት መፍትሔ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በመጨረሻም የኬፕ ታውንና አካባቢው የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ አደረጃጀት ለክብርት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ያዘጋጁትን ስጦታ በኮሙኒቲው ሊቀ መንበር አቶ ታገሰ ሌምባሞ አማካይነት አስረክበዋል።