News

Previous Next

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውን ችግር መፍታት የሚያስችል አበረታች ምላሽ ከሀገሪቱ መንግስት መገኘቱ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የነበሩት / / ዐቢይ አህመድ ከሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው። በውይይቱ ወቅት / / ዐቢይ አህመድ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውን ዜጎች ጉዳይ ዙሪያ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር የመከሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለቀድሞው የደቡብ አፍሪካ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ያደረገችውን ልዩ ድጋፍ በማስታወስ፣ በሀገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሁለንተናዊ መብታቸው ተከብሮ መኖር እንዲችሉ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለፕሬዚዳንቱ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት አግኝተዋል። በተጨማሪም በተደረገው ውይይት በሀገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውን ችግር ለመፍታት የሀገሪቱ መንግስት አበረታች ምላሽ ከመስጠቱም በላይ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በኩል ኮሚቴ አቋቁሞ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርስን ማንኛውም ችግር በማጣራት እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቋል። ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ተወካዮች ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚወያዩበት ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከሁለትዮሽ ውይይቱ አስቀድሞ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የንግድ፣ የሙያ የሀይማኖት ማህበረሰብ መሪዎችና ተወካዮች ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል። ከሁለትዮሽ ውይይቱ በኋላም  በጆሐንስበርግ ከተማ ኢምፔሪያል ዎንደረርስ ክሪኬት ስታዲየም በመገኘትም በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መልዕክት አስተላልፈዋል። በዚህም ወቅት በደቡብ አፍሪከ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በላባቸው ሰርተው የሚያድሩር ጠንካራ እና ሀገር ወዳድ ዜጎች መሆናቸው በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጭምር የሚታወቅ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት የዳያስፖራ ማህበር በዜጎች አንድነት፣ መተሳሰብ እንዲሁም መተባበር ዙሪያ የሚያከናውነውን ተግባር ያደነቁ ሲሆን፣ ይህ ተሞክሮ በሌሎች ሀገራት ዳያስፖራዎች እንደ አርኣያ የሚወሰድ እንደሆነም አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በአፍሪካ ሀገራት የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቅቀው ማምሻውን ወደሃገራቸው መመለሳቸው ይታወቃል።

Previous Next

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ፣ የሶማሌ ክልል መንግሥትና የክልሉ ዳያስፖራ አባላት በኢንቨስትመንትና ዳያስፖራ ተሳትፎ  ዙሪያ የተወያዩበት መድረክ በጅግጅጋ ከተማ መካሄዱ ተገለጸ።

 

የሶማሌ ክልል መንግሥት ከክልሉ ዳያስፖራ ኢንቨስተሮች ጋር በክልሉ ባሉ የኢንቨስትመንት እድሎችና በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ መስጠፌ ሙሀመድ ባስተላለፉት መልዕክት የክልሉ ዳያስፖራዎች በክልሉ እየተከናወነ ባለው ዘርፈ ብዙ የኢንቬስትመንት ሥራ እንዲሳተፉ ጋብዘው፣ የክልሉ መንግሥትም ከጎናቸው እንደሚቆምና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል። በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ /ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስም በበኩላቸው  ክልሉ ዳያስፖራውን በማሳተፍ ለሚያከናውነው ስራ ኤጀንሲው ከጎናቸው እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

 

በተያያዘ ዜና የኤጀንሲው /ዋና ዳይሬክተር በጅግጅጋ በነበራቸው ቆይታ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ መስጠፌ ሙሀመድ ጋር በጽ/ቤታቸው በመገኘት በክልሉ የዳያስፖራ ተሳትፎና በውጭ ሀገራት የሶማሌ ዳያስፖራ ማህበረሰብን በተሻለ መልኩ ማስተባበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከሩ ሲሆን፣ ከክልሉ የዳያስፖራና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ እንዲሁም በመደራጀት ላይ ካለው የክልሉ የዳያስፖራ ማህበር መስራቾች ጋር ተወያይተዋል።

 

Previous Next

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በደቡብ ክልል ልማት ላይ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከክልሉ ም/ፕሬዝዳንት አቶ ርስቱ ይርዳው ጋር ተወያየ።

በውይይቱ ላይ በኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የተመራው የኤጀንሲው ቡድን የተሳተፈ ሲሆን፣ በክልሉ የዳያስፖራ ተሳትፎን ማሳደግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ተዳሰዋል። ከነዚህም መካከል በክልሉ ተጀምረው የተቋረጡ የዳያስፖራ ፕሮጀክቶች ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ ስለማስቀጠል፣ ዳያስፖራው ሊሳተፍባቸው የሚችሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን አጥንቶ ስለማቅረብ፣ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች ገንዘባቸውን በሕጋዊ መልኩ መላክ የሚችሉባቸው መንገዶችን ስለማፈላለግ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ  መሰማራት የሚፈልጉ የዳያስፖራ አባላት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ መሳተፍ የሚችሉበትን ዕድል ስለማመቻቸት ይገኙባቸዋል።

በመጨረሻም ሁለቱም አካላት በክልሉ የዳያስፖራውን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና እንቅስቃሴ  ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጋራ ለመስራትና የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት የተስማሙ ሲሆን፣ በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክም ጉብኝት አድርገዋል።

 

Previous Next

ከዚህም ጋር በተያያዘ በኖርዌይ ኦስሎ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማትን በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ለሊቱን ሲገልጹ ማደራቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ፡፡

ኢትዮጵያዊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ ባረፉበት ግራንድ ሆቴል ተገኝተው ነው ደስታቸውን ሲገልጹ የነበሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይም ደስታቸውን ለመግለፅ በሆቴሉ ለተገኙ ኢትዮጵያዊያን ምስጋና እና ሰላምታ አቅርበዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል እጩነት ፊርማ ከማሰባሰብ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከዳያስፖራው ከፍተኛ ድጋፍ በመደረግ ላይ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሁነቱ የተፈጠረውን ስሜት በፌስቡክ ገጻቸው ሲገልጹ፣ “ኦስሎ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እስክትመስል ድረስ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና በኢትዮጵያ ባነሮች ተውባ ሰነበተች፡፡ ሚዲያዎች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ በኩራት መሰከሩ፡፡” ብለዋል።

ዶክተር አቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማትን በኦስሎ በተካሄደ ስነ ስርዓት በሚቀበሉበት ወቅት ባደረጉት ንግግር “ሰላም እንደ ዛፍ ችግኝ ነው፤ ችግኝን ተክሎ ለማሳደግ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ሰላምም ጥሩ ልብ እና እንክብካቤ ያስፈልገዋል” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና የጠቅላይ ሚኒስትሩን የኖቤል ሽልማት አስመልክቶ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የሃይማኖትና የማህበረሰብ ተወካዮች የተገኙበት ዝግጅት ተካሂዷል። በወቅቱም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የኖቤል ሽልማቱን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለሰላም ባሳዩት ቁርጠኝነት የተገኘና እውቅናውም ለመላው ኢትዮጵያዊያን የተሰጠ መሆኑን ገልጸው፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሰላም ዘብ እንዲቆምና በሚችለው ሙያ ሁሉ ሃገሩን እንዲደግፍ አሳስበዋል። በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍፁም አረጋ በበኩላቸው፥ የኖቤል ሽልማቱ እስካሁን ከተመዘገቡ ድሎች ባሻገር በቀጣይ ከዚህ ለላቀ ስኬት ለመስራት የሚያግዝ ስንቅ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አመራሮች በመላው ዓለም የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነገው ዕለት አዲስ አበባ ሲገቡ የጀግና አቀባበል እንደሚደረግላቸው ለማወቅ ተችሏል።

Previous Next

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበርን ለረዥም አመታት በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ዶ/ር አለባቸው በየነ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ዶ/ር አለባቸው በየነ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ቀደምት መስራቾች አንዱ የነበሩ ሲሆን፣ ለረዥም አመታትም ማህበሩን በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል። ህይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስም ማህበሩን በቦርድ አማካሪነት ሲያገለግሉ ነበር።

በማዕድንና ኤነርጂ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው የነበሩት ዶ/ር አለባቸው፣ ባለፈው ቅዳሜ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም በተወለዱ በ68 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ዶ/ር አለባቸው የአንዲት ሴትና  የሁለት ወንዶች ልጆች አባት ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲም በዶ/ር አለባቸው በየነ ሞት የተሰማውን ሃዘን እየገለጸ፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል።

የቀብር ስነ-ስርዓታቸውም ዛሬ ከቀኑ በ8:00 ሰዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል የሚፈጸም መሆኑን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበበር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

Previous Next

በጀርመን ሃገር ነዋሪ በሆኑት ወ/ት መሰረት አምባው የተቋቋመው ዶቼ ሆህሹለ ፎር ሜዲሲን የህክምና ኮሌጅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር ከተማ የትውውቅ ፕሮግራም አካሄደ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፣ በተጋባዥ እንግዳውና በኮሌጁ ባለቤት መልዕክቶች ተላልፈዋል። የዕለቱ የክብር እንግዳና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ ባለሃብቷ የተወለዱበት አካባቢ ያለበትን ችግር ተረድተውና መፍትሔ የሚሆን ዕቅድ ይዘው ለማልማት በመምጣታቸው አመስግነው፣ ሌሎችም የእሳቸውን አርአያ እንዲከተሉ ጋብዘዋል። ምክትል ከንቲባው አክለውም ከተማ አስተዳድራቸው የዳያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማገዝ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። የድርጅቱ መስራችና ባለቤት ወ/ት መሰረትም በበኩላቸው የክልሉ ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ላደረገላቸው ትብብር ምስጋናቸውን ገልጸው፣ የትውውቅ ፕሮግራሙ ያስፈለገበትን ምክንያት በዝርዝር አቅርበዋል። ከነዚህም መካከል ኮሌጁን ከባለድርሻ አካላት ጋር ማስተዋወቅ፣ ኮሌጁ የህክምና ዶክተሮችን የሚያሰለጥን እንደመሆኑ መጠን በጤናው ዘርፍ በክልሉ ብሎም በሃገር አቀፍ ደረጃ ሊያሳካ ያቀዳቸውን ዓላማዎች ማጋራት እንዲሁም በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሚኖር ግንኙነት መሰረት መጣል የሚሉት ይገኙበታል።

ኮሌጁ ለጊዜው በተከራየው ባለአምስት ፎቅ ህንጻ ውስጥ ስራውን ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ከመጪው የፈረንጆች አዲስ አመት ጀምሮ የማስተማር ስራውን እንደሚጀምር ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ ባለሃብቷ በባሕር ዳር ከተማ የማስተማሪያ ሆስፒታል የመገንባት ዕቅድ እንዳላቸው ታውቋል።

ባለሃብቷ በጀርመን ሃገር በጥብቅና እና በሕግ ማማከር ስራ የሚተዳደሩ ሲሆኑ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ በሃገራቸው በጤናው ዘርፍ የሚታየውን ችግር የመፍታት ህልም እንደነበራቸው ይናገራሉ።

Previous Next

ላለፉት ስምንት ዓመታት በሐዋሳ ከተማ ሊገነባ ታስቦ በልዩ ልዩ ምክንያት ሲጓተት የቆየው ዘመናዊ የገበያ ማዕከልና የቢሮዎች ህንጻ ግንባታን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ከሳውዘርንጌት ኢንቨስትመንት አ/ማ የተገኘው መረጃ አመላከተ።

የሳውዘርንጌት ኢንቨስትመንት አ/ማ በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትይጵያውያን በህብረት ያቋቋሙት የቢዝነስ ማህበር ሲሆን፣ በሐዋሳ ከተማ ዘመናዊ የገበያ ማዕከልና የቢሮዎች ህንጻ ኮምፕሌክስ ለማስገንባት እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቶ የቅድመ ዝግጅት ስራውን አጠናቋል። ፕሮጀክቱ ካለው ግዝፈትና ፋይዳ አንጻር ባለድርሻ አካላትና የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የግንባታ ስራው ሕዳር 20 ቀን 2012 ዓ/ም በይፋ ይጀመራል።

ፕሮጀክቱ ወደ ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር የተበጀተለት፣ በ10ሺ ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ፣ በአንድ መቶ ሰባስድስት የአክሲዮን ማህበር አባላት የተቋቋመና ደረጃ በደረጃ እያደገ የሚሄድ መሆኑን ከአክስዮን ማህበሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

Previous Next

የኖቤል የሰላም ሽልማት ስነ ስርዓት በዛሬው እለት በኖርዌይ ኦስሎ በመካሄድ ላይ ይገኛል ።

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

ባለፈው መስከረም 30 በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።

ዶክተር ዐቢይ ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀው የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ኮሚቴው መግለፁ የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም ሁሉም ባለደርሻ አካለት በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሰላም እና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋፀኦ እውቅና ለመስጠትም እንደተመረጡ ኮሚቴው ገልጿል።

ኮሚቴው በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማምጣት ቃል መግባታቸውን በማስታወስ፥ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበል ሀገራቱ አስመራ ላይ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ማስቻላቸውን ነው ያነሳው።

ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ስምምነት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻክሮ የነበረው የጅቡቲና ኤርትራ ግንኙነት እንዲስተካል ሚና እንደነበራቸው አስታውሷል።

የኖቤል ኮሚቴው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለረጅም አመታት የነበረው ውጥረት እንዲፈታ ተነሳሽነት ሲወስዱ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ሀሳቡን በበጎ መልኩ ተቀብለዋል ብሏል።

ከዚህ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ በርካታ ለውጦችን በመካሄድ የሀገሪቱ ዜጎች ለተሻለ ህይወት ተስፋ እንዲያደርጉ አድርገዋል ብሏል ኮሚቴው።

ምንጭ፡- ፋና ብርድካስቲንግ ኮርፖሬት

Previous Next

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዳያስፖራዎች በፋይናንስ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባንኮች ጋር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሄደ።

በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር / ሰላማዊት ዳዊት በተመራው የውይይት መድረክ ላይ የመንግስትና የግል ባንኮች የስራ ሃላፊዎች በተሳታፊነት የተገኙ ሲሆን፣  የኤጀንሲው ተግባርና ሃላፊነት እንዲሁም የዳያስፖራ ተሳትፎን ለማሳደግ በኤጀንሲው እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ቀርበዋል። ባንኮችም በበኩላቸው ለዳያስፖራ ስላመቻቿቸው ፓኬጆች፣ስለሚሰጧቸው የአገልግሎት አይነቶች፣ ከዳያስፖራ የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ እያጋጠሟቸው ስላሉ ተግዳሮቶችና መወሰድ አለባቸው ባሏቸው የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

ከዳያስፖራ የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በባንኮቹ ከተጠቀሱ ተግዳሮቶች መካከል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት አለመዳበር፣ በመንግስታዊ ተቋማት የሚወጡ መመሪያዎች በየጊዜው መለዋወጥ፣ ዳያስፖራዎች የተሳሳተ መረጃ ይዘው የባንክ አገልግሎቶችን መጠየቅና ምላሹም አሉታዊ በሚሆንበት ወቅት ቅሬታ ፈጥሮ መሄድ፣ ሊያከናውኑ ላሰቡት ስራ የሚሆን በቂ ካፒታል ሳይይዙ የባንክ አገልግሎትን መጠየቅ እንዲሁም የተንዛዛ ቢሮክራሲያዊ አሰራር መኖር ጥቂቶቹ ናቸው።

በባንኮቹ የቀረቡትን ተግዳሮቶች አስቀድሞ በመገንዘብ ኤጀንሲው በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሯ አብነቶችን በማንሳት ያብራሩ ሲሆን፣ በቀጣይም ችግሮቹ እስኪቀረፉ ድረስ ኤጀንሲው ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በመጨረሻም የመድረኩ ተሳታፊዎቹ የግንኙነት ጊዜያቸውን ስለመወሰን፣ የዳያስፖራ ፋይናን አገልግሎትን በተመለከተ ከኤጀንሲው ጋር በቅንጅት መስራት ስለሚቻልበት ሁኔታና የዳያስፖራ ባንክ አገልግሎቶችን የሚያስተዋውቅ የጋራ ቡክሌት ስለማዘጋጀት በቀረበው ምክረ-ሃሳብ ላይ በሙሉ ድምጽ በመስማማት ውይይታቸውን አጠናቀዋል።

Previous Next

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር የመዋቅርና የአሰራር ችግሮችን በመቅረፍ ሁሉንም የክልል ዳያስፖራ ማህበራትን የሚወክል አቋም እንዲኖረው በማስቻል ላይ ያተኮረ የክልል ዳያስፖራ ማህበራት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄደ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት መድረኩን ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኤጀንሲው ማህበራትን መደገፍ በሃላፊነት ከተሰጡት ተግባራት አንዱ መሆኑን አንስተው፣ የማህበራት ተወካዮቹ በጋራ በመስራት ኢትዮጵያን የሚመስል ማህበር በመመስረት በጎ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችልና እርስ በእርሱ በመናበብ ለላቀ ዓላማ የሚተጋ አደረጃጀት እንደሚፈጥሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የማህበራት ተወካዮቹም ማህበሩ ሊኖረው በሚገባው የተስተካከለ መዋቅርና አሰራር ዙሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል። በመድረኩ ከተንጸባረቁ ሃሳቦች መካከልም ነባሩ ማህበር ያሉት ጠንካራ ጎኖች ተወስደው፣ የተበላሹና መልካም ያልሆኑት ተትተው፣ የተሻለ ነገር መገንባት ይገባል የሚለው አንዱ ሲሆን፣ በሌለም በኩል አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከየክልሉ በተውጣጡ ተወካዮች አማካኝነት እንደአዲስ ይደራጅ የሚል ይገኝበታል። የመድረኩ ተሳታፊዎችም በቀረቡት ሃሳቦች ላይ ሰፊ ጊዜ ወስደው ተወያይተውባቸዋል። በመጨረሻም ተወካዮቹ በደረሱበት ስምምነት መሰረት በአንድ ሰብሳቢና ጸሐፊ የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም በአንድ ወር ጊዜ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ሊከተላቸው የሚገቡ የአደረጃጀት አማራጮችንና ስልቶችን ለይተው ያለቀለት ምክረ-ሃሳብ ለኤጀንሲው ለማሳወቅ ተስማምተዋል።

ከሳምንታት በፊት ተካሂዶ በነበረው የፌዴራልና የክልል የዳያስፖራ ባለድርሻ አካላት መድረክ ላይ በሃገር ውስጥ የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበር አደረጃጀቶችን ማጠናከር የሚቻልበት ሁኔታ በአጀንዳነት ተይዞ ውይይት እንደተደረገበት መዘገባችን ይታወሳል።

Previous Next

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች በመድንና በአነስተኛ ፋይናንስ ዘርፍ እንዳይሰማሩ የሚከለክለውን ህግ ለማንሳት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አፀደቀ።

እንደ ፋና ብሪድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘገባ አዋጁ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በመድን ስራ እና በአነስተኛ ፋይናንስ ዘርፍ ላይ እንዳይሳተፉ የተጣለውን የህግ እገዳ በማንሳት በዘርፉ መዋእለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚፈቅድመሆኑን በላይ፣ በስራ ላይ አስቸጋሪ ሆነው ከተገኙ የአዋጁ አንቀጾች መካከል በአጭር ጊዜ መሻሻል የሚችሉትን በማሻሻል በአሰራር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም በዘርፉ በተሰማሩ አካላት ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑ ተብራርቷል።

የምክር ቤቱ አባላት ክልከላው መነሳቱ ስለሚያስገኘው ጠቀሜታ፣ ዘርፉን እንዲቆጣጠር የተቋቋመው አካል ስላለው አቅም ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ክልከላው መነሳቱ በተለይም ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቅረፍ አይነተኛ ሚና እንዳለውና የመቆጣጠር አቅምን ማሳደግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የህግ ማዕቀፎችም በስራ ላይ እንዳሉ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ምክር ቤቱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በባንክ ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚፈቅደውን አዋጅ ከወራት በፊት ማጽደቁ ይታወሳል።

Previous Next

ላለፉት ስምንት ዓመታት በሐዋሳ ከተማ በሳውዘርንጌት ኢንቨስትመንት አክሲዮን ማህበር ሊገነባ ታስቦ በልዩ ልዩ ምክንያት ሲጓተት የቆየው ዘመናዊ የገበያ ማዕከልና የቢሮዎች ህንጻ ኮምፕሌክስ  ፕሮጀክት የግንባታ ስራ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የፕሮጀክቱ ተወካዮች በተገኙበት በይፋ ተጀመረ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የታደሙት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ኤጀንሲው የተቋረጡ የዳያስፖራ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል በትጋት እየሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎችም ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። የአክሲዮን ማህበሩ ተወካዮችም በበኩላቸው መሰል ፕሮጀክቶችን በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ላይ ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸው፣ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር በልዩ ልዩ የመንግስት አካላት ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ፕሮጀክቱ በአንድ መቶ ሰባ ስድስት የአክሲዮን ማህበር አባላት የተቋቋመና በ10ሺ ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ ወደ ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተያዘለት መሆኑን ከአክስዮን ማህበሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ፕሮጀክቱ ደረጃ በደረጃ እያደገ የሚሄድና ልዩ ልዩ ግንባታዎችን የሚያካትት መሆኑን ያገኘነው መረጃ አክሎ ገልጿል።

የፕሮጀክቱ ባለቤት ሳውዘርንጌት ኢንቨስትመንት አክሲዮን ማህበር በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትይጵያውያን በህብረት ያቋቋሙት የቢዝነስ ማህበር መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።