ዜና

Previous Next

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የተመራ የልዑካን ቡድን በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያየ

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የተመራ የኤጀንሲው የልዑካን ቡድን በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበራትና አደረጃጀት መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር ተወያየ፡፡
በመድረኩም በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው፣ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን ለመደገፍ እያደረጉ ስላለው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትም መድረኩ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተወካዮች ጋር በመወያየት የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማትና ተሳትፎ ስራዎችን ለማጠናከር ብሎም ከዚህ አንጻር እያጋጠሙ ያሉ ማነቆዎችን በመለየት መፍትሔ ለማፈላለግ መመቻቸቱን ገልጸው፣ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለሃገራዊ ፕሮጀክቶችም ሆነ ወቅታዊ ጥሪዎች እያደረጉ ላሉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በኤጀንሲው እየተከናወኑ ያሉ ዋና ዋና ስራዎችና የተገኙ ውጤቶች፣ የመደራጀት ጠቀሜታ እንዲሁም በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰነድ የቀረበ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም ለውይይት በመነሻነት እንዲያገለግል በቀረበው ሰነድ ላይ ተመስርተው ላነሷቸው ጥያቄና አስተያየቶች ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለውይይት መነሻ በቀረበው ሰነድ ላይ በመመስረት በተሳታፊዎች ከቀረቡ ሃሳቦች መካከልም በደቡብ አፍሪካ በህጋዊነት ለመኖር እንዲችሉ ከዚህ በፊት ተጀምረው የተቋረጡ የወረቀት ስራዎች ቀጥለው በህጋዊ መንገድ ገንዘብ ወደ ሃገር ቤት መላክ የሚችሉበት ሁኔታ ሊመቻችላቸው እንደሚገባ፣ በቀውስ ወቅት የፖለቲካ ልዩነትን የተሻገረና ሃገራዊ ጥቅምን ያስቀደመ አንድነት ሊፈጠር እንደሚገባ፣ ዳያስፖራው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን፣ ከወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እየተሰራጩ ያሉ የተሳሳቱና ጎጂ መረጃዎችን ለመመከት የዘመቻ ስራ የሚያከነውን አካል አቋቁመው በመስራት ላይ መሆናቸውን፣ ዳያስፖራውን በቤቶች ልማት ፕሮግራም ላይ ለማሳተፍ ሊሰራ እንደሚገባ፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የሚያስችሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው፣ ጥምር ዜግነት የማግኘት ጉዳይ እንዲሁም ባሉበት ሆነው በሃገራዊ ምርጫ የመሳተፍ ዕድል ሊመቻችላቸው እንደሚገባ ማንሳታቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡