ዜና

Previous Next

በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ‘ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም’ የሚለውን ሃሳብ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍና የውይይት መድረኮች አካሄዱ

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ምክር ቤት አስተባባሪነት በመመራት በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና ልዩ ልዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ‘ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም’ የሚለውን ሃሳብ በመቃወም “ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ አለች፡፡ ኢትዮጵያ ትኖራለች፡፡” በሚል ርዕስ ሰላማዊ ሰልፍና የውይይት መድረኮችን አካሄዱ፡፡
‘የኢትዮጵያዊነት ድምጽ’ በሚል መሪ መልዕክት ስር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው በተለያዩ የዓለም ከተሞች በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፍና የውይይት መድረኮች ላይ የኢትዮጵያዊነትንና የህብረ-ብሄራዊነትን ውበት የሚያንጸባርቁ በርካታ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡ ከነዚህ መካከልም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከዘር-ሐረግ፣ ከፓለቲካ ፓርቲ፣ ከሀይማኖት ድርጅት፣ ከሥልጣን እንዲሁም ከማንኛውም የግልና የቡድን ፍላጎቶች በላይ መሆኑ፣ ኢትዮጵያ የተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖች የተከሏት እና ጉዳያቸዉን ሲጨርሱ የሚያፈርሷት ጊዜያዊ ድንኳን ሳትሆን በአባቶቻችንና በእናቶቻችን ደምና አጥንት የተገነባችና ማንም ሰው ለግሉና ለቡድኑ ጥቅም ሲል እንዲያፈርሳት እንደማይፈቀድ፣ ስርዓት አልበኝነትን ለመግታት መንግስት እያካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር ሂደት እንደሚደግፉ፣ በህግ ቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎችም በፍርድ ቤት ጥፋተኛ እስኪባሉ ድረስ መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ፣ ለተጀመሩ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ አድናቆትና አክብሮት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ሃብት ለማሰባሰብ ከዚህ በፊት ያደርጉ ከነበረው አስተዋጽኦ በላይ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸው ይጠቀሳሉ፡፡
በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከተዘጋጁ መድረኮች መካከል በኖርዌይ ኦስሎ የውይይት መድረክ ላይ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ባስተላለፉት መልዕክትም ዳያስፖራው ከየትኛውም ቡድናዊ ፍላጎት በላይ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለማስከበር የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ዳያስፖራው ሃገራዊ ፕሮጀክቶች የሆኑትን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን፣ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚደረገው ጥረትን እንዲሁም ‘ገበታ ለሃገር’ን ለመደገፍ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው፣ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ምክር ቤቱ በሃገር ህልውና እና ክብር ላይ የሚቃጡ አደጋዎችን ከመከላከል በተጨማሪ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚሳኩ ትልልቅ ውጥኖችን ይዞ በመስራት ላይ የሚገኝ መሆኑን የሚጠቁም ሲሆን፣ ዳያስፖራውን በማስተባበር ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን መደገፍና የተሳካላቸው የሌሎች ሃገር ዳያስፖራዎችን ተሞክሮ በመቀመር ዳያስፖራው በሃገራዊ ዕድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ማድረግ የሚሉት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡