ዜና

Previous Next

ከኮቪድ-19 መከሰት ጀምሮ ዳያስፖራው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገበ።

አዲስ አበባ መስከረም 27/2013 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰትን ተከትሎ ዳያስፖራው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በታህሳስ 2012 ዓ.ም በቻይናዋ ውሃን ከተማ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ደረጃ በመዛመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ይዟል፤ መቶ ሺዎችንም ሕይወት ቀጥፏል።

በኢትዮጵያም መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ከቡርኪናፋሶ የመጣ ጃፓናዊ በኮሮናቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያ ሰው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ቫይረሱ አሁንም በመስፋፋት ላይ ነው።

ይህን ተከትሎ ወረርሽኙ በተለያየ መልኩ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ሀብት የሚያሰባስብ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሙ ወደ ስራ መግባቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ይገልጻሉ።

በብሔራዊ ኮሚቴው ስር ንዑሳን ኮሚቴዎች መቋቋማቸውንና ኤጀንሲውም ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ ሀብት የሚያሰባስበውን ኮሚቴ እየመራ የተለያዩ ተግባራትን እየከወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳያስፖራውም ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ሩብ ዓመት 100 ሚሊዮን ብር ገደማ በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ማድረጉን ነው ለኢዜአ የገለጹት።

በሩብ ዓመቱ ለመሰብሰብ የታቀደው ሀብት 50 ሚሊዮን ብር እንደሆነና የተገኘው ሀብት ከታቀደው ከእጥፍ በላይ እንደሆነም ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የተናገሩት።

በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በወረርሽኙ ሳቢያ ይገጥማቸዋል ተብሎ ከሚጠበቀው ኢኮኖሚያዊ ጫና አንጻር ያደረጉት ድጋፍ ከተገመተው በላይ ነው ብለዋል።

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለሕክምና ባለሙያዎችና ለማኅበረሰቡ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና መሳሪያዎችን በመለየትና ግዥ በመፈጸም ወደ አገር ቤት እየላከ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተለይም የሕክምና ባለሙያዎች ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፉ በተጨማሪ የሕክምና ባለሙያ የሆኑ ዳያስፖራዎች የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ሙያዊ ድጋፍ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ምሁራንም መድረኮችን በመፍጠር ኮቪድ-19 የሚያደርሳቸውን ጉዳቶች በመተንተንና መፍትሔዎችን በማቅረብ ላይ እንደሆኑም ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት።

ምሁራኑ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስመልክቶ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ለመንግስት ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን እያቀረቡ እንደሆነም አክለዋል።

በሌላ በኩል ከወረርሽኙ መከሰት ጋር ተያይዞ በተለያዩ አገራት በተለይም በመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ የሚገኙ ዜጎችን ባሉበት የመደገፍ፤ የከፋ ችግር ያጋጠማቸውንም ወደ አገር ቤት የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት መግታትና መቆጣጠር የሚያስችሉ መፍትሔ ጠቋሚ ምክረ ሀሳቦች የሚቀርቡባቸው መድረኮችና የጥናትና ምርምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በሙያና በጥናትና ምርምር እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲቀጥልም ወይዘሮ ሰላማዊት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።