ዜና

Previous Next

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማውን በቢሾፍቱ ከተማ አደረገ፡፡
የግምገማ መድረኩን የከፈቱት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ባስተላለፉት መልዕክት መድረኩ የተዘጋጀው ያለፉትን ሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም በመገምገም ጥንካሬዎች ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉበት የታዩ ክፍተቶችም የሚሞሉበት ሁኔታን ለመፍጠር እንዲሁም በሌሎች ተጨማሪ አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት መሆኑን ገልጸው፣ ተሳታፊዎች በሚቀርቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ከኤጀንሲው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ከቀረቡ ዋና ዋና ጉዳዮችም በሩብ ዓመቱ 12.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 336 የዳያስፖራ ኢንቨስተሮች የምልመላና የድጋፍ አገልግሎት መሰጠቱ፣ 825 ዳያስፖራዎች የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲከፍቱ በማድረግ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ ማድረጋቸው፣ ዳያስፖራውን በማስተባበር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ለገበታ ለሃገር ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም ለኮቪድ-19 መከላከያ ከ194 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ መቻሉ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ተሳተፊዎችም በቀረበው የስራ አፈጸጻም ሪፖርት ላይ የክልል ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን ከመገደፍ፣የሚሲዮን ክላስተሮችን ከማጠናከር እንዲሁም ከድጋፍ በዘለለ ለዳያስፖራ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ የተደረገ ድጋፍ ያስገኘውን ውጤት ከመከታተል አንጻር ጥያቄና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ በተቋሙ የስራ ሃላፊዎችና አመራሮች ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡
ከሩብ ዓመቱ የስራ አፈጻጸም በተጨማሪ በመድረኩ የቀጣይ ሁለት ወራት የስራ ክፍሎች ቼክሊስትና የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ሰነድ ቀርበው በውይይት ዳብረዋል፡፡ በማግስቱም የኤጀንሲው ሰራተኞችና አመራሮች የእንጦጦ ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡
Previous Next

ነዋሪነታቸውን በአሜሪካን ሃገር ያደረጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት TASFA የተባለው ተቋም ዓመታዊ የባለሙያዎች ቨርቹዋል ኮንፈረንስ የመክፈቻ ፕሮግራሙን አካሄደ።
ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር አቶ ፍጹም አረጋ ባስተላለፉት መልዕክት የተከፈተ ሲሆን፣ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት የሚገኙ ከመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል። ሁለቱም ሃላፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት ዳያስፖራው ሃገሩን በዕቅወቱ፣ በክህሎቱና በገንዘቡ ለመደገፍ እያደረጋቸው ያሉት እንቅስቃሴዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን አብነቶችን በማንሳት ገልጸው፣ ይኸው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ኮንፈረንሱ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መካከል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በሃይል አቅርቦት፣ በልዩ ትምህርት፣ በሆስፒታሊቲና ቱሪዝም እንዲሁም በልዩ ልዩ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የዕውቀት፣ የመልካም ተሞክሮዎችና ልምዶች ሽግግር መፍጠርን ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱን የተቋሙ አስተባባሪ ዶ/ር ደረጀ ተሰማ ገልጸዋል፡፡
በኮንፈረንሱ መርሃ ግብር መሰረት በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በተለዩት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ልምዱና ተሞክሮው ያላቸው የተቋሙ አባላት ገለጻ የሚያደርጉ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች ለሚነሱ ጥያቄዎችም ከመድረክ ምላሽ የሚሰጥባቸው ይሆናል።

በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት ዳያስፖራው ወደ አገሩ ከሚልከው ገንዘብ 4 ቢሊዮን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ 50 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም ገልጿል።

የዓለም ባንክ ባደረገው ጥናት እ.አ.አ በ2019 በተለያዩ የዓለም አገሮች የሚኖሩ ዜጎች ወደ አገራቸው 712 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ (ሬሚታንስ) መላካቸውን ገልጿል።

አብዛኛው ገንዘብም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገራት የተላከ መሆኑንም አመልክቷል።

ይኽው መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ከሚገኙ ዘጠኝ ሰዎች አንዱ ከሬሚታንስ በሚገኝ ገንዘብ ድጋፍ የሚያገኝ ሲሆን በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ዜጎችም በወር በአማካይ ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ወደ አገራቸው ይልካሉ።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ አፍሪካዊያን 48 ቢሊዮን ዶላር የላኩ ሲሆን ናይጄሪያ፣ጋና ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን በዋንኛነት ገንዘቡ ከተለካባቸው አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

ከሦስት እስከ አምስት ሚሊዮን ዜጎቿ በተለያዩ የዓለም አገራት ይኖራሉ ተብሎ የምትገመተው ኢትዮጵያም ዜጎቿ በተለያዩ የፋይናንስ አማራጮች ገንዘባቸውን ወደ አገራቸው ይልካሉ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ዳያስፖራው ወደ አገር ውስጥ ከሚልከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) 4 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የታቀደው ዕቅድ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሬሚታንስ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ያስገባና ለዚህም ዳያስፖራው ሕጋዊ አማራጮችን ተጠቅሞ ወደ አገሩ ገንዘቡን እንዲልክ የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

“በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የባንክ ቅርንጫፎችን የመክፈትና ሕጋዊ አሰራሮችን ተግባራዊ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ ነው” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ገንዘብ ሁሉም ሬሚታንስ ተብሎ እንደሚቀመጥና ኤጀንሲው ከዚህ ውስጥ ዳያስፖራው ወደ አገሩ የላከውን ገንዘብ ከባንኩ ጋር በመሆን የመለየት ተግባር በመከናወን ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የመለየት ተግባሩ ዳያስፖራው ለግለሰብ የሚልከውንና የዳያስፖራ ድርጅት አገር ውስጥ ለሚገኝ ድርጅት የሚልከውን ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል። 

የአዲሱ የብር ኖት መቀየርም ሕገወጥ የገንዘብ አላላክ ሂደት አፍርሶ ህጋዊ የፋይናስ አሰራርን ለመከተል ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሰማራ የተለያዩ አማራጮችንና እድሎችን የማስተዋወቅ እንዲሁም ወደ አገር ቤት በሚመጣበት ወቅት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከተቋቋመባቸው አላማዎች መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

በ2013 በጀት ዓመትም 50 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ ኤጀንሲው እቅድ መያዙን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት። 

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ 300 ዳያስፖራዎች  በተለያዩ መስኮች ሊሰማሩባቸው የሚችሉባቸውን አማራጮች በአካል መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ዳያስፖራዎቹ ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ሰሜን አሜሪካና አፍሪካ የመጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ግብርና፣ ቱሪዝምና አምራች ዘርፍ ዳያስፖራዎቹ ወደ ሥራ ቢገቡባቸው ውጤታማ ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ መስኮች እንደሆኑና በሚያገኙት ጥቅም ላይ ገለጻ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም አመልክተዋል።

“ዳያስፖራው አማራጮችን ያያል፤ ፍላጎት አለው ማለት ሁሉም መዋዕለ ንዋዩን ያፈሳል ማለት አይደለም” ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት፣ በተጨባጭ የመስራት ፍላጎት ያላቸው ወደ ኢንቨስትመንት እንደሚገቡ አመልክተዋል።

አንድ ዳያስፖራ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ስራ መግባት ከፈለገ ለፕሮጀክቱ ከሚያወጣው ካፓታል 25 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንዳለበትም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እያፈሰሱ ያሉ ዳያስፖራዎች ያቋቋሟቸው ማህበራት በአሁኑ ወቅት በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ላሳዩ ዳያስፖራዎች ተሞክሯቸውን እያካፈሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ መዘግየትና ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዳያስፖራው ሊፈቱ ይገባል ብሎ ያነሳቸው ተግዳሮቶች እንደሆኑም ገልጸዋል።

የተጠቀሱት ችግሮች ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እንዲበጅላቸው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ወይዘሮ ሰላማዊት አመልክተዋል።

መንግስት ሰላምና ደህንነትን ለማስከበር በትኩረት እየሰራ መሆኑንና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መዘግየት እንዳይኖር በየጊዜው እየተፈተሸ የመፍትሔ  እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና በሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የልማት ስራዎች የዳያስፖራውን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲሁም መብታቸው እንዲጠበቅ ተልዕኮ ተሰጥቶት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በመጋቢት 2011 ዓ.ም ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል።

በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት አጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ ከተላከው 8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላሩ ከዳያስፖራዎች የተላከ መሆኑን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

እ.አ.አ በ2020 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢኮኖሚ ላይ ባሳደረው ጫና ምክንያት ከውጭ አገር የሚላክ ገንዘብ መጠን (ሬሚታንስ) በ20 በመቶ እንደሚቀንስ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ያሳያል።

Previous Next

የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ለዳያስፖራው በቀረበው የድጋፍ ጥሪ መሰረት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ቀጥለዋል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ 23 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 3.3 ሚሊዮን የእጅ ጓንቶችን እንዲሁም በሲያትል የኮቪድ-19 አስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አሰባሳቢ ግብረ ሃይል ደግሞ 135,000 ዶላር የሚያወጡ ልዩ ልዩ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን አስረክበዋል። ርክክቡ በተካሄደባቸው ጊዜያትም የጤና እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የስራ ሃላፊዎችና ድጋፉን ያሰባሰቡ የዳያስፖራ አደረጃጀት ተወካዮች መገኘታቸውን ማወቅ ተችሏል።
ኮቪድ-19 የጋረጠውን አደጋ ለመከላከል ለዳያስፖራው በቀረበው ሃገራዊ ጥሪ መሰረት እስከ አሁን ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ድጋፍ በአይነትና በገንዘብ መሰብሰብ መቻሉ ይታወሳል።
Previous Next

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ምክር ቤት አስተባባሪነት በመመራት በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና ልዩ ልዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ‘ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም’ የሚለውን ሃሳብ በመቃወም “ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ አለች፡፡ ኢትዮጵያ ትኖራለች፡፡” በሚል ርዕስ ሰላማዊ ሰልፍና የውይይት መድረኮችን አካሄዱ፡፡
‘የኢትዮጵያዊነት ድምጽ’ በሚል መሪ መልዕክት ስር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው በተለያዩ የዓለም ከተሞች በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፍና የውይይት መድረኮች ላይ የኢትዮጵያዊነትንና የህብረ-ብሄራዊነትን ውበት የሚያንጸባርቁ በርካታ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡ ከነዚህ መካከልም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከዘር-ሐረግ፣ ከፓለቲካ ፓርቲ፣ ከሀይማኖት ድርጅት፣ ከሥልጣን እንዲሁም ከማንኛውም የግልና የቡድን ፍላጎቶች በላይ መሆኑ፣ ኢትዮጵያ የተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖች የተከሏት እና ጉዳያቸዉን ሲጨርሱ የሚያፈርሷት ጊዜያዊ ድንኳን ሳትሆን በአባቶቻችንና በእናቶቻችን ደምና አጥንት የተገነባችና ማንም ሰው ለግሉና ለቡድኑ ጥቅም ሲል እንዲያፈርሳት እንደማይፈቀድ፣ ስርዓት አልበኝነትን ለመግታት መንግስት እያካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር ሂደት እንደሚደግፉ፣ በህግ ቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎችም በፍርድ ቤት ጥፋተኛ እስኪባሉ ድረስ መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ፣ ለተጀመሩ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ አድናቆትና አክብሮት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ሃብት ለማሰባሰብ ከዚህ በፊት ያደርጉ ከነበረው አስተዋጽኦ በላይ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸው ይጠቀሳሉ፡፡
በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከተዘጋጁ መድረኮች መካከል በኖርዌይ ኦስሎ የውይይት መድረክ ላይ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ባስተላለፉት መልዕክትም ዳያስፖራው ከየትኛውም ቡድናዊ ፍላጎት በላይ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለማስከበር የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ዳያስፖራው ሃገራዊ ፕሮጀክቶች የሆኑትን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን፣ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚደረገው ጥረትን እንዲሁም ‘ገበታ ለሃገር’ን ለመደገፍ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው፣ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ምክር ቤቱ በሃገር ህልውና እና ክብር ላይ የሚቃጡ አደጋዎችን ከመከላከል በተጨማሪ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚሳኩ ትልልቅ ውጥኖችን ይዞ በመስራት ላይ የሚገኝ መሆኑን የሚጠቁም ሲሆን፣ ዳያስፖራውን በማስተባበር ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን መደገፍና የተሳካላቸው የሌሎች ሃገር ዳያስፖራዎችን ተሞክሮ በመቀመር ዳያስፖራው በሃገራዊ ዕድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ማድረግ የሚሉት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
Previous Next

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚያገለግሉና 135,000 ዶላር የሚያወጡ ልዩ ልዩ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን አሰባስበው ከመጡ የሲያትል የኮቪድ-19 አስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አሰባሳቢ ግብረ ሃይል አባላት ጋር ውይይት አደረገ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ለእንግዶቹ የእኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ኤጀንሲው ከተቋቋመ ጀምሮ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት እንዲሁም በኤጀንሲው ውስጥ የሚገኙ አበይት የስራ ክፍሎችንና ተልዕኳቸውን አስተዋውቀዋል።
የግብረ ሃይሉ አባላትም በበኩላቸው በሲያትልና አካባቢዋ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር እየሰሯቸው ስላሉ ስራዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የዳያስፖራውን ልዩ ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባና በሃገር ውስጥ የዳያስፖራውን ስራ የሚያሳልጥ ኤጀንሲ መኖሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፤ ከዳያስፖራ አንጻር መፈታት አለባቸው ባሏቸው ጉዳዮችም ላይ ጥያቄና አስተያየት አቅርበዋል።
በተለይም የግብረ ሃይሉ ቡድን መሪ ፓስተር ብርሃኑ ወልደማሪያም ግብረ ሃይሉ ለኮቪድ-19 ሃብት ከማሰባሰብ በተጨማሪ ሌሎች ሃገራዊ አጀንዳዎችን ለማሳካት ራዕይ ሰንቆ በመስራት ላይ እንዳለ ገለጻ አድርገዋል። ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው የአሜሪካን ከተሞች ተዘዋዋሪ የችቦ ማብራት መርሃ ግብር በማካሄድና ሃብት በማሰባሰብ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መደገፍ እንደሚገኝበት ገልጸዋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትና ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ መሐምድ እንድሪስም የግብረ ሃይሉ አባላት ላሳዩት ተነሳሽነትና የሃገር ፍቅር ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፣ ግብረ ሃይሉ የሚያከናውናቸውን ስራዎች ለመደገፍም ሆነ ከዳያስፖራ ተሳትፎ አንጻር የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ለመፍታት ኤጀንሲው ሁልጊዜ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ለግብረ ሃይሉ አባላት ክብር ኤጀንሲው የምሳ ግብዣ ፕሮግራም ያዘጋጀ ሲሆን፣ ግብረ ሃይሉ ወደ አሜሪካ ከመመለሱ በፊት ታላቁ ተኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብንና በጣና ሃይቅ ላይ የተጋረጠውን የዕንቦጭ አረም ችግር በአካል በመገኘት እንደሚመለከት ለማወቅ ተችሏል።
Previous Next

በተያዘው ዓመት ከዳያስፖራው ለ”ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት” 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ክልል ወንጪና በደቡብ ክልል ኮይሻ የሚገኙ አካባቢዎችን ለማልማት በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም የ “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክትን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለፕሮጀክቱ ድጋፍ በማድረግ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ ማቅረባቸውም አይዘነጋም።

ይህን ተከትሎ የተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ለ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ፕሮጀክቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙንና በስሩ የዳያስፖራውን ጉዳይ የሚመለከት ንዑስ ኮሚቴም ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በ2013 ዓ.ም ዓመት ከዳያስፖራው ለፕሮጀክቱ 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።

በዕቅዱ ለመሰብሰብ የታሰበውን ገንዘብ ለማሳካት በፕሮጀክቱ የታቀፉትን ኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪን ለዳያስፖራው በተለያዩ አማራጮች የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነና ይሄም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በ “ገበታ ለሸገር” የተሰሩ ሥራዎችን ለዳያስፖራዎች የማስጎብኘት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና ይህም ዳያስፖራዎች “ገበታ ለሀገር ” ፕሮጀክትም ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት እንዲያድርባቸው አድርጓል ብለዋል።

ከዳያስፖራው የሚገኘውን የገንዘብ ድጋፍ በተቀመጠው አሰራር መሰረት ለብሔራዊ ኮሚቴው ገቢ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ የ “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ላይ ድጋፉን በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ወይዘሮ ሰላማዊት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዳያስፖራው ለፕሮጀክቱ ድጋፍ እንዲያደርግ በከፈተው 0100101300591 የባንክ ሒሳብ ቁጥር (አካውንት) ገቢ ማድረግ እንደሚችልም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዳያስፖራው በኢትዮጵያ በሚከናወኑ ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶችና የልማት ሥራዎች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ወይዘሮ ሰላማዊት ጥሪ አቅርበዋል።

“ገበታ ለሸገር” ወደ “ገበታ ለሀገር” የተሸጋገረ ሲሆን ሸገርን በማስዋብ ፕሮጀክት የተገኘውን ልምድ በአገር ደረጃ በማሳደግ “ ገበታ ለሀገር” በሚል ጎርጎራ፣ ወንጪና ኮይሻ የማስዋብ ፕሮጀክቶች ለማሳካት እቅድ ተይዟል።

ለሦስቱ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ቢያንስ ስድስት ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና ከባለሃብቶች፣ ከህብረተሰቡና ዳያስፖራው ሦስት ቢሊዮን ብር ይሰባሰባል ተብሎ ይጠበቃል።

ቀሪው ገንዘብ ደግሞ ከልማት አጋሮች ለመሰብሰብ ታቅዷል።

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ መነሻ ሃብት ለማሰባሰብም 10 ሚሊዮን እና አምስት ሚሊዮን ብር የሚከፈልበት የእራት ግብዣዎች በገበታ ለሀገር መርሃ ግብር በጥቅምት ወር ይዘጋጃሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በኢትዮ- ቴሌኮም አማካኝነት የአጭር የጽሁፍ መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያ እንዲሁም ድጋፍ እንዲደረግ ገንዘብ የሚሰበሰብበት የባንክ ሒሳብ ቁጥር ይፋ መደረጉም የሚታወስ ነው።

Previous Next

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አመራርና ሰራተኞች ለ’ገበታ ለሃገር’ ፕሮጀክት የወር ደሞዛቸውን ለገሱ።
የኤጀንሲው ሰራተኞች በዛሬው ዕለት ባካሄዱት ውይይት የ’ገበታ ለሃገር’ ፕሮጀክትን ሃገራዊ ፋይዳ በመረዳት በዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ የወር ደሞዛቸውን የለገሱ ሲሆን፣ ኮቪድን በመከላከል ስራቸውን በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚያከናውኑም ገልጸዋል።
መድረኩን የመሩት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትም ሰራተኞች ወቅታዊውን የኑሮ ጫና ተቋቁመው የ’ገበታ ለሃገር’ ፕሮጀክትን ለመደገፍ ላሳዩት ፍላጎት ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ ወደ መደበኛ የስራ ሁኔታ መገባቱን አንስተው፣ ሰራተኞች በኤጀንሲው የተዘጋጀውን የኮቪድ-19 መከላከያ ፕሮቶኮል በጥንቃቄና ሁልጊዜ በመተግበር ራሳቸውንና ተገልጋዮችን ከኮቪድ ወረርሽን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
Previous Next

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በ2013 በጀት አመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ።

ዳያስፖራው በዚሁ ሩብ ዓመት ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱንም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታውቋል።

ግንባታው በራስ አቅም ለሚከወነው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀብት ማሰባሰብ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ የነበሩ ችግሮች የዳያስፖራውን ተሳትፎና ድጋፍ አቀዛቅዞት እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይሁንና ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በግድቡ የዲፕሎማሲ በተለይም በሶስትዮሽ ድርድሩ የኢትዮጵያ አቋምና የመጀመሪያ ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት በዳያስፖራው ላይ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸዋል።

ይህን አጋጣሚ በመጠቀምም ዳያስፖራው በተቀናጀ መንገድ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረግ የሚችልበትን ሁኔታ በመፍጠር ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

በዚህም በ2013 በጀት አመት  የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት ለኢዜአ የገለፁት።

ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪም ዳያስፖራው በሩብ ዓመቱ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል ነው ያሉት።

እየተደረገ ያለው ድጋፍ ዳያስፖራው በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ ያለው እምነት እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክት ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ።

እንደ ወይዘሮ ሰላማዊት ገለፃ በተያዘው በጀት ዓመት ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ 200 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዷል።

ዳያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ የሚያደርግባቸው አማራጮችን የማስፋት ስራም እየተከናወነ ነው።

ከዳያስፖራው ሐብት ለማሰባሰብ ኤጀንሲው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ባንኮች፣ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተ ቡድን ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።

ከገንዘብ ድጋፉ ባሻገር ኢትዮጵያ በግድቡና በአጠቃላይ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስረዳት ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን አቋም የሚያስረዳ ቋሚ መድረክ መፈጠሩንና ይህም ዘላቂነት ባለው መልኩ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ወይዘሮ ሰላማዊት የዳያስፖራው ማኅበረሰብ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጉዳይ በሚገባ ተረድቶ የማስተዋወቅ ስራ እንዲሰራ በሩብ ዓመቱ ለተለያዩ ግለሰቦች ስልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል።

ግድቡን አስመልክቶ የኢትዮጵያን አቋም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስረዳት እየተከናወነ ያለው ተግባር የአገራትና ተቋማትን አመለካከት እየቀየረ መምጣቱን፤ ይህም መልካም ጅምር እንደሆነ አብራርተዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ745 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 71 ሚሊዮን 431 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ከግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ13 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የዳያስፖራው ድርሻ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ነው።

Previous Next

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ‘ገበታ ለሀገር’ ፕሮጀክት ያለበትን እንቅስቃሴ በተመለከተ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ገለጻ አደረገ።
በገለጻው ላይ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋችው፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክቡር ኢንጂነር ዶ/ር አብርሃም በላይ፣ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጄኔራል ማናጀር ኢንጂነር ሃበታሙ ተገኝ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል።
ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርም ባለፈው ዓመት በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስርትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ሃሳብ አፍላቂነት የሸገር ፓርክ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጎ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ደረጃውን የጠበቀ ፓርክ ተገንብቶ መመረቁን አስታውሰው፣ የዛሬው ገለጻ ዓላማ በዚህ ዓመት ‘በገበታ ለሀገር’ ፕሮጀክት ወደ ትግበራ የሚገቡትን የኮይሻ፣ የወንጪ እና የጎርጎራ ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ እና የቀጣይ አቅጣጫ በተመለከተ ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ባለፈው ዓመት የሸገር ፕሮጀክት ይፋ ሲደረግ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ እንደማይቻል ስጋት የነበረ ቢሆንም፣ በሃገር ውስጥና በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ፣ አጋር ሃገሮች፣ የዲፕሎማተክ ማህበረሰቡ እና የበላይ አመራሩ የላቀ ቁርጠኝነት በማሳየታቸው ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ለፍጻሜ መብቃቱን ገልጸው ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፤ እንደ ሸገር ፕሮጀክት ሁሉ የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ በ'ገበታ ለሀገር’ ፕሮጀክቶች ላይም ተመሳሳይ ተሳተፎ በማደረግ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የክቡር ሚኒስትሩን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ በኢፌዲሪ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ክቡር ኢንጂነር ዶ/ር አብርሃም በላይና በኢትዮጵያ መንገዶቸ ባለስልጣን ጄኔራል ማናጀር ኢንጂነር ሃብታሙ ፕሮጀክቶቹን ወደ ትግባራ ምዕራፍ ለማስገባት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል፤ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሾች ተሰጥተዋል።
ገለጻዎቹን ተከትሎ ከሚዲያ አካላት ጋር በነበረው ቆይታ ‘የገበታ ለሀገር’ ፕሮጀክት የውጭ ሀብት አሰባሳቢ ንኡስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን በተለመከተ በክብርት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፣ በተለይም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ በኮቪድ-19 መከላከልና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ በ’ገበታ ለሃገር’ ላይም እንደሚደግመው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በመጨረሻም ’የገበታ ለሀገር’ ፕሮጀክትን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማሳካት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚዲያዎች ጋር የሚኖረውን ቀጣይ አንቅስቃሴ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ክቡር አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች ተጨማሪ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
Previous Next

አዲስ አበባ መስከረም 27/2013 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰትን ተከትሎ ዳያስፖራው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በታህሳስ 2012 ዓ.ም በቻይናዋ ውሃን ከተማ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ደረጃ በመዛመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ይዟል፤ መቶ ሺዎችንም ሕይወት ቀጥፏል።

በኢትዮጵያም መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ከቡርኪናፋሶ የመጣ ጃፓናዊ በኮሮናቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያ ሰው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ቫይረሱ አሁንም በመስፋፋት ላይ ነው።

ይህን ተከትሎ ወረርሽኙ በተለያየ መልኩ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ሀብት የሚያሰባስብ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሙ ወደ ስራ መግባቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ይገልጻሉ።

በብሔራዊ ኮሚቴው ስር ንዑሳን ኮሚቴዎች መቋቋማቸውንና ኤጀንሲውም ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ ሀብት የሚያሰባስበውን ኮሚቴ እየመራ የተለያዩ ተግባራትን እየከወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳያስፖራውም ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ሩብ ዓመት 100 ሚሊዮን ብር ገደማ በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ማድረጉን ነው ለኢዜአ የገለጹት።

በሩብ ዓመቱ ለመሰብሰብ የታቀደው ሀብት 50 ሚሊዮን ብር እንደሆነና የተገኘው ሀብት ከታቀደው ከእጥፍ በላይ እንደሆነም ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የተናገሩት።

በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በወረርሽኙ ሳቢያ ይገጥማቸዋል ተብሎ ከሚጠበቀው ኢኮኖሚያዊ ጫና አንጻር ያደረጉት ድጋፍ ከተገመተው በላይ ነው ብለዋል።

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለሕክምና ባለሙያዎችና ለማኅበረሰቡ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና መሳሪያዎችን በመለየትና ግዥ በመፈጸም ወደ አገር ቤት እየላከ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተለይም የሕክምና ባለሙያዎች ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፉ በተጨማሪ የሕክምና ባለሙያ የሆኑ ዳያስፖራዎች የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ሙያዊ ድጋፍ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ምሁራንም መድረኮችን በመፍጠር ኮቪድ-19 የሚያደርሳቸውን ጉዳቶች በመተንተንና መፍትሔዎችን በማቅረብ ላይ እንደሆኑም ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት።

ምሁራኑ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስመልክቶ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ለመንግስት ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን እያቀረቡ እንደሆነም አክለዋል።

በሌላ በኩል ከወረርሽኙ መከሰት ጋር ተያይዞ በተለያዩ አገራት በተለይም በመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ የሚገኙ ዜጎችን ባሉበት የመደገፍ፤ የከፋ ችግር ያጋጠማቸውንም ወደ አገር ቤት የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት መግታትና መቆጣጠር የሚያስችሉ መፍትሔ ጠቋሚ ምክረ ሀሳቦች የሚቀርቡባቸው መድረኮችና የጥናትና ምርምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በሙያና በጥናትና ምርምር እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲቀጥልም ወይዘሮ ሰላማዊት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።