የዳያስፖራ ተሳትፎ ማስፋፋትና ማጠናከር

የዳያስፖራ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት እስከ አሁን ከነበሩ ተሞክሮዎች እና አሁን ላይ ከሚፈለገው የዳያስፖራው የተሳትፎ አይነትና የወደፊት አስፈልጎት በመነሳት ቁልፍ በሆኑ የተሳትፎ አይነቶች የተደራጀ ነው፡፡ በዳይሬክቶሬቱ ስር የንግድ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም የስራ ክፍል አንዱ ቁልፍ የስራ ክፍል ነው፡፡ ዳያስፖራው በሀገር ቤት ለሚያካሂደው የንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከኤጀንሲው የሚሰጡ ግልጋሎቶችን በአንድ መስኮት እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ በቱሪዝም እና ሀገር ማስተዋወቅ ስራ ላይ ለሚሰማሩ የዳያስፖራ የቱሪዝም ድርጅቶች እና የዳያስፖራ ማህበራት በሀገር ቤት የዳያስፖራውንና በዳያስፖራው አስተባባሪነት ለሚዘጋጁ ሀገር የማስተዋወቅ ፕሮግራሞች የሚጫወቱትን ሚና ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በሀገራችን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች በዳያስፖራው ማህበረሰብ እንዲጎበኙ እና እንዲለሙ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ይቀርፃል፣ ያስተባብራል፡፡

የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የስራ ክፍል ኤጀንሲው ከዚህ በፊት በተበታተነ መልኩ የነበሩ ተሞክሮዎችን ወደ አንድ በማምጣትና በማጠናከር ከሚሰራባቸው የስራ ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር በተለይም  ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከኢኖቬሽንን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ለሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዳያስፖራውን በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግሩ ዘርፍ ጉልህ ሚና እንዲጫወት የሚያስተባብር የስራ ክፍል ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎች እና ሌሎች የትምህርት እና የስልጠና ተቋማት ስራዎቻቸውን በማዘመኑ ረገድ ከዳያስፖራውና በዳያስፖራው አስተባባሪነት ከሚገኙ የሌሎች ድርጅቶች ድጋፎች አማካኝነት የማገዝ ስራዎችን ያስተባብራል፡፡ ከንግድ እና ኢንቨስትመንት ተሳትፎዎች የሚቀሰሙ ምርጥ ተሞክሮዎችን በተደራጀ መልኩ በመያዝ በሀገር ቤት ለማስፋትና ለማሰራጨት የሚያስችሉ መንገዶችን ከሚመለከታቸው ተቋማትጋር በጋራ ይሰራል፡፡

የሀብት ማሰባሰብና ፕሮጀክት የስራ ክፍል ሶስተኛው ሲሆን በዋናነት የሀብት ምንጮችን የማስፋት እና አስቀድመው በሚቀረፁ ፕሮጀክቶች በመታገዝ በሀገር ልማት ላይ አስተዋፅኦ ማድረግን ያለመ የስራ ክፍል ነው፡፡ የተለየዩ የዳያስፖራ ኮሚኒቲዎችን በሀገር ቤት በተመረጡ ትናንሽ እና መካከለኛ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፉ ይሰራል፡፡ የዳያስፖራ ማህበራት ከተለያዩ የሲቪክ ሶሳይቲ ፈንድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የፕሮጀክት አሰራሮችን ያስተዋውቃል ድጋፍም ያደርጋል፡፡ በኤጀንሲ ደረጃ በተለያዩ የዳያስፖራ የህብረተሰብ ክፍሎች (ለምሳሌ በህፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች) ጋር የተያያዙ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና ሀብት በማሰባሰብ እንዲሰሩ ያስተባብራል፡፡ ተመላሽ ዳያስፖራዎች በሀገር ቤት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የውስጥ አቅማቸውን በማስተባበር እና ከውጭ ተጨማሪ ሀብት በማሰባሰብ ለህብረተሰቡ የሚጠቅሙ የበጎ አድራጎት ስራዎችን እንዲሰሩ የፕሮጀክት ቀረፃ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ የኤጀንሲውን ሰራተኞች እንዲሁም ከኤጀንሲው ስራ ጋር ተያያዥ ለሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የአቅም ግንባታ ስራ የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን ያከናውናል፡፡ የክልል ማስተባበሪያ /ቤቶችን ለማጠናከርም ክልሎች ከሚመድቡት በጀት በተጨማሪ በፕሮጀክት በመታገዝ ሀብት በማሰባሰብ የማጠናከር ስራ ይሰራል፡፡ የሚገኙ ተጨማሪ ሀብቶች የሚውሉባቸውን ስራዎች በቋሚነት ይከታተላል፡፡ በአጠቃላይ ኤጀንሲው ጠንካራ ተቋም ሆኖ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ የሀብት ምንጮችን ማስፋትና የተሸለ ተሞክሮ ለማግኘት ይህ የስራ ክፍል በልዩ ትኩረት ይሰራል፡፡

የዳያስፖራ ማህበራትና በጎ አድራጎት የስራ ክፍል በውጭ ሀገር እና በሀገር ቤት የዳያስፖራ ማህበራት እንዲጠናከሩ ይሰራል፡፡ ለማህበራቱ የሙያ፣ የሀብት አማራጫቸውን የሚያሰፉባቸው መንገዶች እና ህግ ነክ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ በዳያስፖራው አስተባባሪነት በትምህርት፣ በጤና፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና በሌሎች ዘርፎች በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ዜጎችን በበጎ ፈቃድ ስራ ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ያስተባብራል፡፡ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚኖሩ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን የመሰረቷቸው ማህበራት መካከል ህብረት እንዲፈጠር ይሰራል፡፡ ማህራቱ በሀገር ቤት የማህበረሰብ አገልግሎቶች እንዲሰጡ ያበረታታል ሁኔታዎችንም ያመቻቻል፡፡ በኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበራት የሚገጥሟቸውን ችግሮች እንዲቀረፉ ህግ ነክ እና መመሪያ የሚፈልጉ ስራዎችን ያስፈፅማል፡፡ በሀገር ቤት የሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበራት ከዳያስፖራ ማህበራት ጋር የስራ ትብብር እንዲያደርጉና የአቅም ግንባታ ስራዎች እንዲሰሩ እድሎችን ያመቻቻል፡፡ የዳያስፖራ ማህበራት በሀገር ቤት በስማቸው የተለያዩ የበጎ አድራገቶት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን እንዲመሰርቱና ለነበሩት የገንዘብ፣ የሙያ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ እንዲያጠናክሩ ያስተባብራል፡፡