የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ስራዎች

ይህ ስራ ዳያስፖራውን በሚመለከት ለሚሰሩ ማህራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች እንደ ቅድመ ሁኔታ ሊወሰድ የሚችል ቁልፍ ሚና ነው፡፡ የዳያስፖራ ማሕበረሰባችንን በተመለከተ የምንከተላቸው ፖሊሲዎች እና አቅጣጫዎች በሙሉ ውጤታማነታቸው የሚመሰረተው ጠንካራ የዳያፖስራ ማህበረሰብ እንዲኖረን በምንከተለው ስትራቴጂ ውጤታማነት ልክ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ዳያስፖራው ላይ የተከተልናቸው አቅጣጫዎች የፖሊሲ ክፍተት ሳይኖርባቸው በሚፈለገው መልኩ ዳያስራውን ማስተባበር ያልቻሉት ይህ የማህበረሰብ ልማት ስራ ለዳያስፖራው በሚመጥን አስተሳሰብ እና አደረጃጀት ከወቅሩ ጋር በሚጣጣም መልኩ ባለመሰራቱ ምክንያት ነው፡፡ የዳያስፖራውን መብትና ጥቅም ማስከበር እንዲሁም ሀገራችን ከዳያስፖራው ልታተርፍ የሚገባትን የልማት አጋርነት ለማረጋገጥ በቅድሚያ ዳያስራውን መረዳት እና በርሱ ላይም ሰፊ ስራ መስራት ይጠይቃል፡፡ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰባችንንም የሚኖሩበት ሀገርን ነባራዊ ሁኔታ ባገነዘበ ነገር ግን በሃገር ጉዳይ ተቀራራቢ በሆነ ግንዛቤና ስሜት ለማስተባበር የሚቻለው የማህበረሰብ ልማት ስራውን ነባራዊውን ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሲሰራ ነው፡፡ ተመሳሳይ ሚናዎች በሁሉም ሀገራት ባሉ የዳያስፖራ ማህረሰባችን ሊሰራ እንደማይችለው ሁሉ ተመሳሳይ የማስተባበሪያ ስትራቴጂም ለሁሉም ዳያስፖራ ሊውል አይችልም፡፡
ክልሎችም በራሳቸው የሚያደርጓቸው ዳያስፖራ ነክ ስራዎች በተለይም የዳያስፖራ outreach programs በራሳቸው የሚበረታቱ ቢሆኑም አጠቃላይ እንዲፈጠር ከሚፈለገው የዳያስፖራ ማህበረሰብ ሀገራዊ ገፅታ፣ ሀገራዊ መግባባት እና በሀገር ልማት ጉዳይ ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤ እንዲሁም ኤጀንሲው እንደ ፌዴራል ተቋም የሚካሄዱ ዳያስፖራ ነክ ስራዎችን የማወቅ፣ የመደገፍ እና የተደራጀ ሪፖርት የማጠናቀር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ከዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ስራዎች ጋር እንዲቀናጁ ቢደረግ ስራውን በከፍተኛ ሁኔታ ያቀላጥፈዋል፡፡ በመሆኑም የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ስራችን ማህበረሰቡ ያለበትን የህግ፣ የኢኮኖሚ አቅም፣ የባህል እና እምነት ነባራዊ ሁኔታዎች በሚገባ በሚረዳ እና ይህንንም ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስተባበር ያለመ ነው፡፡ ይህም ስራ ከኤጀንሲው ተልእኮ ከዋነኞቹ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ ተደራጅቷል፡፡

በዚሁ የስራ ክፍል በዳያስፖራ ማሕበረሰባችን መካከል አገራዊ መግባባትን የሚፈጥር፣ ብዝሃነትን የተቀበለ አገራዊ ማንነትን የማጎልበት፣ የመቻቻል እና አብሮነት ባህልን የማዳበር፣ ዳያስፖራው ከሚኖርባቸው አገራት ለአገራዊ እሴት ግንባታ የሚረዱ ልምዶችን ለሀገሩ የሚያስተላልፍበት መድረኮችን የሚያመቻች፣ በዳያስፖራው እና ሀገር ቤት ባለው ዜጋ መካከል አገራዊ መስተጋብር ማጠናከር እና የመሳሰሉት ተግባራትን ያከናውናል፡፡ በማህበረሰብ ውስጥ ያሉ  ባህላዊና ሀይማኖታዊ በአላት እንደ ትልቅ ሶሻል ካፒታል በመጠቀም ዳያስፖራውን የዕርስበርስ ትስስሩ እንዲጠናከር ይሰራል፡፡ በተጨማሪም በአገራችን እንዲመጣ የሚፈለገው የፖለቲካ ባህል ለውጥ እና አጠቃላይ የፖለቲካ ሪፎርም ዳያስፖራውን ያሳተፈና ለተሸለ የፖለቲካ ባህል፣ ለጠንካራ የዴሞክራሲ ግንባታ እና ሀገራዊ መግባባት የሚያግዙ ስራዎችን ይሰራል፡፡

ከዚህ ሌላ በዚሁ የስራ ክፍል የሴቶችና ወጣቶች የተመለከቱ በኤጀንሲው ሆነ በውጭ ሀገር በሚገኙ የዳያስፖረ ክፍል ስራዎችን አስመልክቶ መብታቸውን የማስጠበቅ፣ Gender streaming ሥራ የሚሰሩ ይሆናል ከዚህ ጋር ተያይዞም በሴት የዳያስፖራ አባላት የሚቋቋሙ የዳያስፖራ ማህበራትን የመደገፍ፣ አገር ቤት ካሉ ተመሳሳይ ማህበራት ጋር የማገናኘት እና በጋራ ለሀገር ልማት የሚሰሩበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስራዎችን ይሰራሉ። በተጨማሪም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ትውልድ የሆነውን ወጣት ዳያስፖራ በተለያዩ አገርህን እወቅ እና የመሳሰሉት ፕሮጀክቶችን የመቅረፅ እና የማሳተፍ ስራዎች በዚሁ የስራ ክፍል የሚተገበሩ ይሆናሉ