የመረጃ፣ ጥናትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

የዳያስፖራ ማሕበረሰባችንን በሚመለከት ከቁጥር ጀምሮ የተሟላ እና ተዓማኒ የሆነ መረጃ አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ስለ ዳያስፖራ ማሕበረሰባችን የተሰሩ የዳሰሳ ጥናቶችም በአሃዝ የተደገፉ ባለመሆናቸው ለአቅጣጫ እና ዕቅድ መነሻ የመሆን አቅማቸው ደካማ ነው፡፡ የዳያስፖራ ገዳይ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መረጃ የሚሰበሰብበት ሁኔታ ቢኖርም የመስሪያ ቤቶቹ የተቀናጀ አሰራር አለመኖር እንደ ሀገር ማጣቀሻ መሆን የሚችል የዳያስፖራ መረጃ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ይህንን ችግር ሊፈታ የሚጠበቅበትና ተግባርና ኃላፊነቱም የሆነው ደግሞ የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ኤጀንሲ ነው፡፡ ኤጀንሲው ከየትኛውም ወገን በተሸለ እና በተደራጀ መልኩ መረጃ የመሰብሰብ፣ የመተንተን እና የማሰራጨት ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ለመንግስት የፖሊሲ ግብአት የሚውሉ ዳያስፖራ ነክ መረጃዎች እና ጥናቶች ማቅረብም ኤጀንሲው በተቀዳሚነት ሊወጣው የሚገባው ተግባር ነው፡፡ በሌሎች ተቋማት በተበታተነ መልኩ የሚሰበሰቡ መረጃዎች መልክ እንዲይዙ እና እንደ ሀገር ተዓማኒ የሆነ በአስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችም የተናበበ ስራ ለመስራት የሚያስችል የመረጃ ማሰባሰብ ዳያሰፖራ ነክ ጥናቶችን ማድረግ ኤጀንሲው በልዩ ትኩረት የሚያከናውነው ተግባር ነው የሚሆነው፡፡
ይህ የስራ ክፍል በሌሎች የስራ ክፍሎች የሚሰበሰቡ መረጃዎች፣ የሚሰሩ ስራዎችን እና የሚቀመሩ ተሞክሮዎችን ይመዘግባል፡፡ ዳታ ቤዝ ማደራጀት፣ መረጃ መተንተንና ተወራራሽ የሆኑ ተቋማዊ የመረጃ ክምችት (Institutional memory) እንዲኖር የማድረግ ስራን ይሰራል፡፡ መረጃዎችን ለሌሎች የስራ ክፍሎች በሚሆን መልኩ ያደራጃል፡፡ የዳያስፖራውን የሀገር ቤት ሚና እና በሚኖሩባቸው ሀገራት ያሏቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ መረጃ ይሰበስባል ፡፡ ዳያስፖራ ነክ የጥናት እና ምርምር ስራዎችን ይሰራል፣ ያስተባብራል፡፡ የዳያስፖራ ጉዳዮች ጥናት ላይ በተመሰረቱ አሰራሮች እንዲመሩ ይሰራል፡፡ የህግ እና ፖሊሲ ማሻሻያዎች አስፈላጊ ሆነው ሲገኙ በጥናት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ይሰራል፡፡ የዳያስፖራውን ሀገራዊ ሚና እና ተግዳሮቶቹን በጥናት በተደገፈ መልኩ ለመንግስት እና ለህዝብ እንዲቀርብ ያስተባብራል፡፡ የኤጀንሲው ሌሎች የስራ ክፍሎች ስራቸውን በመረጃ እና በጥናት ታግዘው እንዲሰሩ ከሁሉም ጋር በመተባበር ይሰራል፡፡ ዳያስፖራውን በሚመለከት በሌሎች ተቋማት የሚሰሩ ጥናቶችን ያሰባስባል የጥናት ውጤቶችንም ለሚለከታቸው የስራ ክፍሎች በሚሆን መልኩ አሰናድቶ ያቀርባል፡፡ ሀገር አቀፍ እና አለምአቀፍ ተቋማት በዳያስፖራው ጉዳይ ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ ጥናቶችን እንዲያካሂዱ ያስተባብራል፡፡
በዚሁ የስራ ክፍል ያለው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኤጀንሲው ባሉት አማራጭ የኮሙኒኬሽን መንገዶች በሙሉ ለተቋማት፣ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ እና ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆን በቋሚነት ይሰራል፡፡ ዳያስፖራውን እና ኤጀንሲውን አስመልክቶ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተደራሽ በሆነ መልኩ መልስ ይሰጣል፡፡ በህትመት ስራዎች እና በሚዲያ ፕሮግራሞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ይሰራል፡፡ በውጭ ሀገራት በኮሚኒቲ ራድዮኖች የተለያዩ የሚዲያ ፕሮግራሞችን በዳያስፖራው አስተባባሪነት እንዲሰሩ ያግዛል፡፡ በሀገር ውስጥ በመንግስም ሆኑ በግል የኤሌክትሮኒክ መገናኛ ዘዴዎች የአየር ሰአቶችን በመግዛት እና ፕሮግራሞችን ስፖንሰር በማድረግ የዳያስፖራውን ሀገራዊ ሚና የማስተዋወቅ እንዲሁም በዳያስፖራው ሀገራዊ ተሳትፎ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ማህበረሰቡ እንዲገነዘባቸው የሚያስችሉ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በዳያስፖራ በሚገኙ የሚዲያ ተቋማት የዳያስፖራውን ሀገራዊ ሚና ሊያሳድግ በሚችል መልኩ እንዲሰሩ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በኤጀንሲው ዌብሳይት፣ ማህበራዊ ሚዲያ እና እንዳስፈላጊነቱ የሚዘጋጁ የህትመት ውጤት የሆኑ የመገናኛ መንገዶችን በቋሚነት በባለቤትነት ይዞ ይሰራል፡፡