የዳያስፖራ ማህበረሰቡን የምንረዳበት እና የምንገልፅበት መንገድ ዳያስፖራውን በአገሩ ልማት እዲሳተፍ እና መንግስም የዳያስፖራው መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት በአይነትም በመጠንም ተፅእኖ ያሳድርበታል፡፡ በአጠቃላይ ኤጀንሲው በአራት መርሆዎች ላይ የተመሰረተ የዳያስፖራ ማህበረሰብ እሳቤን ይዞ ይንቀሳቀሳል፡፡
የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ዳይሬክቶሬት፡- የዳያስፖራውን መብትና ጥቅም ማስከበር እንዲሁም ሀገራችን ከዳያስፖራው ልታተርፍ የሚገባትን የልማት አጋርነት ለማረጋገጥ በቅድሚያ ዳያስራውን መረዳት እና የማህበረሰብ ልማት ስራዎችን መስራት የጠይቃል፡፡ ይህ የስራ ክፍል በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰባችንን የሚኖሩበት ሀገርን ነባራዊ ሁኔታ ባገነዘበ ነገር ግን በሃገር ጉዳይ አካታችና ተቀራራቢ በሆነ ግንዛቤና ስሜት ለማስተባበር የሚያስችሉ የማህበረሰብ ልማት ስራዎችን የሚያስተባብር ነው፡፡
የዳያስፖራ ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት፡- በዳይሬክቶሬቱ የ ንግድ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም የስራ ክፍል አንዱ ቁልፍ የስራ ክፍል ነው፡፡ ዳያስፖራው በሀገር ቤት ለሚያካሂደው የንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከኤጀንሲው የሚሰጡ ግልጋሎቶችን በአንድ መስኮት እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ ዳያስፖራውን በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግሩ ዘርፍ ጉልህ ሚና እንዲጫወት የሚያስተባብር የስራ ክፍል ነው፡፡
የመረጃ፣ ጥናትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፡- በዳያስፖራ ማህበረሰባችን ጉዳይ እና ስለ ዳያስፖራ ማህበረሰባችን ወቅታዊ ሁኔታ ኤጀንሲው ከየትኛውም ወገን በተሸለ እና በተደራጀ መልኩ መረጃ የመሰብሰብ፣ የመተንተን እና የማሰራጨት ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ለመንግስትና ለሚመለከታቸው አካላት የፖሊሲ ግብአት የሚውሉ ዳያስፖራ ነክ መረጃዎች እና ጥናቶች ማቅረብም ኤጀንሲው በተቀዳሚነት ሊወጣው የሚገባው ተግባር በመሆኑ ኤጀንሲው በልዩ ትኩረት የሚያከናውነው ተግባር ነው የሚሆነው፡፡
የዳያስፖራው መብት ማስጠበቅና የህግ ከለላ ዳይሬክቶሬት፡- በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንደ ዜጋ ከመንግስት ሊያገኗቸው የሚገቡ ግልጋሎቶች እና ሊጠበቅላቸው የሚገቡ መብቶች አሏቸው፡፡ የኤጀንሲው መቋቋም አንዱ ትልቁ መነሻም ይኼው የመብት እና ጥቅም ማስከበር ጉዳይ በመሆኑ ከቁልፍ ተግባራቱ አንዱ ይህ እንዲሆን ተደርጓል፡፡